የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመከላከል የሚያግዝ የድንበር ተሻጋሪ የጭነት ተሸከርካሪዎች ተርሚናል ግንባታ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመከላከል የሚያግዝ የድንበር ተሻጋሪ የጭነት ተሸከርካሪዎች ተርሚናል ግንባታ መጀመሩን የትራስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የድንበር ተሻጋሪ የጭነት ተሸከርካሪዎች ተርሚናል ግንባታው በሶማሌ ክልል በሽንሌ ሲቲ ዞን አይሻ ወረዳ ደወሌ ቀበሌ በይፋ መጀመሩንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።
ተርሚናሉ የተሽከርካሪዎች ማቆያ እና በሂደትም ሁሉንም አገልግሎቶች ያካተተ ለአሽከርካሪዎች የመታጠቢያ፣ የማረፊያ፣ የምግብ፣ የጤና ምርመራና ህክምና አገልግሎቶችን የሚሰጥ ነው።
ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት፣ በአንድ ሀገር ክልል ውስጥ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዲሁም ድንበር በር ላይ በሚደርሱባቸው ወቅቶች የሚወስዷቸው ጥንቃቄዎች ለወረርሽኙ ያላቸውን ተጋላጭነት ለመቀነስ ከፍተኛ ሚና አላቸው።
በመሆኑም ተጋላጭነቱን ለማስወገድ ከደቡብ አፍሪካ ቀጠና የልማት ጥምረት፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አማካሪዎች ካውንስልና የጤና ሚኒስቴር እንዲሁም የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ያወጡዋቸውን የአሰራር ስርዓቶችና ሰነዶች መሠረት ያደረጉ ስታንዳርዶችን መጠቀም መቻሉን ተገልጻል፡፡
የኢፌዴሪ ትራንሰፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ ለደወሌ ተርሚናል ግንባታ ስኬት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተገቢውን የድጋፍ፣ የክትትልና የቁጥጥር ስርዓት የዘረጋ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአካባቢው ህብረተሰብና የመስተዳድር አካላት እንደጅምሩ ሁሉ ለግንባታው በስኬት መጠናቀቅ አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርጉ እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።