ኮርፖሬሽኑ የብሪክስ ሀገራትን እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም በሚገባ ለመጠቀም በትኩረት ይሰራል – አቶ አክሊሉ ታደሰ
አዲስ አበባ፣ የካቲት13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አክሊሉ ታደሰ ከግሎባል ኢንዲያ ቢዝነስ ፎረም ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
አቶ አክሊሉ ÷ኮርፖሬሽኑ አሁን ላይ ከህንድ ፣ ከሩሲያ፣ ከቻይናና ከብራዚል ባለሃብቶች፣ ኤምባሲዎችና የኢንቨስትመንት ተቋማት ጋር አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በፓርኮቹ ለመሳብ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይም የብሪክስ አባል ሀገራት ያላቸውን እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም አማጥጦ ለመጠቀም የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የግሎባል ኢንዲያ ቢዝነስ ፎረም ፕሬዚዳንት ጅቴንድራ ጆሺ በበኩላቸው÷ ከህንድ የመጣው ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተለይም በፋርማሲዩቲካልና በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ለመሰማራት የሚያስችል ቅድመ ኢንቨስትመንት መረጃ ማጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑ አባላት በፋርማሲዩቲካል፣አግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በሎጅስቲክስና ቴክስታይል የኢንቨስትመንት ዘርፎች በመስራት ላይ እንደሚገኙ የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
ልዑኩ የቂሊንጦ እና ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክን የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውሮ መጎብኘቱም ተጠቁሟል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በሚያስተዳድራቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮችና ነጻ የንግድ ቀጣና የህንዳውያን ባለሃብቶች ተሳትፎን በየጊዜው እያደገ መምጣቱ ተጠቅሷል፡፡
አሁን ላይ ከ12 በላይ ግዙፍ ኢንቨስትመንት ያላቸው ህንዳውያን ባለሃብቶች በፋርማሲዩቲካል፣ በቴክስታይል እና በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፎች ላይ በመሰማራት ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ እድል ፈጥረዋል፡፡