Fana: At a Speed of Life!

በእነ ወንደሰን አሰፋ (ዶ/ር) መዝገብ ተካተው ያልቀረቡ ተከሳሾች የጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸው ታዘዘ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሽብር ወንጀል በተከሰሱት እነ ወንደሰን አሰፋ (ዶ/ር) መዝገብ ተካተው ያልቀረቡ ተከሳሾች የጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግላቸውና እንዲቀርቡ ታዘዘ።

ትዕዛዙን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ የህገ መንግስትና በህገ መንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከተው ችሎት ነው።

ችሎቱ በዛሬው ቀጠሮ ከአማራ ክልል ጋር ተያይዞ በሽብር ወንጀል በተከሰሱት እነ ወንደሰን አሰፋ (ዶ/ር) መዝገብ ተካተው ባልቀረቡ ምሬ ወዳጆን ጨምሮ 27 ተከሳሾች የጋዜጣ ጥሪ እንዲደረግና እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል ችሎቱ ከዚህ በፊት በነበረ ቀጠሮ ዐቃቤ ህግ ባቀረበው አቤቱታ ማለትም በማረሚያ የሚገኙ ወንደሰን አሰፋ (ዶ/ር)፣ መስከረም አበራን ጨምሮ 23 ተከሳሾች የፍርድ ቤቱ አካባቢን በጩኸት በማወክ ረብሸዋል በሚል ምክንያት በአካል ሳይቀርቡ ክርክራቸውን በቪዲዮ ኮንፍረንስ እንዲያደርጉ እንዲታዘዝለት ባቀረበው አቤቱታ ላይ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የተከሳሾች ጠበቆች በዐቃቤ ህግ የቀረበው ችሎት ሳይቀርቡ ባሉበት በቪዲዮ ኮንፍረንስ ክርክራቸውን እንዲያደርጉ ያቀረበው አቤቱታ የህግ አግባብነት እንደሌለው ጠቅሰው መልስ ሰጥተዋል።

ፍርድ ቤቱም መርምሮ ተከሳሾቹ ስነ-ስርዓታዊ ህጉን ተከትለው ክርክር ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝቧል።

በህገመንግስቱ በተሰጠ መብት መሰረት ተከሳሾች በአካል ቀርበው የመከራከር መብታቸውን ፍርድ ቤቱ ከግምት ውስጥ ማስገባቱን ጠቅሶ፤ በድጋሚ የፍርድ ቤቱን ስርዓት የሚጥስ ተግባር እንዳይፈጽሙ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል።

በድጋሚ ፈጽመው ቢገኙ ግን ያለምንም ቅድመ ሀኔታ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ችሎቱ ገልጾ ብይን ሰጥቷል።

በዚህ መልኩ ፍርድ ቤቱ የጋዜጣ ጥሪ ለመጠባበቅና ከዚህ በፊት ዐቃቤ ህግ በክስ ዝርዝሩ ላይ ጉዳት ደረሰባቸው የተባሉ ግለሰቦች ማንነትን በማካተት አሻሽሎ እንዲያቀርብ በተሰጠ ትዕዛዝ መሰረት ውጤቱን ለመጠባበቅ ለሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.