በወምበራ ወረዳ ከ155 ሚሊየን ብር በላይ የተገነቡ ሁለት የመንገድ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በወምበራ ወረዳ ከ155 ሚሊየን ብር በላይ የተገነቡ ሁለት የመንገድ ፕሮጀክቶችን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን መርቀው ከፍተዋል።
የመንገድ ፕሮጀክቶቹ በወምበራ ወረዳ ከደብረዘይት – ሳንቂ – መልካን እና ከገሰንገሳ – ወግዲ የሚያገናኙ ናቸው።
ለትራፊክ ክፍት ከተደረጉት መንገዶች ከገሰንገሳ – ወግዲ ቀበሌ የሚያገናኘው መንገድ የ11 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ ደብረዘይት – ሳንቂ – መልካን ቀበሌዎችን የሚያገናኘው የመንገድ ፕሮጀክት ደግሞ 33 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መሆኑም ተገልጿል፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቶቹን መርቀው የከፈቱት የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ “መንግስት የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች በመመለስ ላይ ነው” ብለዋል፡፡
የመንገዶቹ መጠናቀቅ፣ ምርታማ ለሆኑት እና በተፈጥሮ ለታደሉት አካባቢዎች የላቀ ጠቀሜታ እንዳላቸው ጠቁመው፣ የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማሳደግ እንደሚያግዝም ርዕሰ-መስተዳድሩ መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ህብረተሰቡ ለሠላምና ለልማት ሥራዎች ትኩረት መስጠትና መተባበር ይጠበቅበታል ያሉት አቶ አሻድሊ፣ መንግስት ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ እየሠራ ያለውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡
የክልሉ መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቀልቤሳ ወልጅራ፣ የደብረዘይት – ሳንቂ – መልካን የመንገድ ፕሮጀክት በ64 ሚሊዮን 626 ሺህ ብር በክልሉ በጀት የተገነባ ሲሆን፣ ከገሰንገሳ – ወግዲ የሚያገናኘው ደግሞ ከኢፌዴሪ የሠላም ሚኒስቴር በተገኘ 90 ሚሊዮን 638 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ መገንባቱን ተናግረዋል፡፡