የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ከጀመርንበት ጀምሮ ወሳኝ ርምጃዎች ተራምደናል – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዟችንን ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ እንደ ሀገር ወሳኝ ርምጃዎችን ተራምደናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የፌደራል እና የክልሎች ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የመካከለኛ ዘመን ግምገማ ተካሂዷል፡፡
በዚሁ ወቅትም ለዕቅዱ መነሻ የሆኑ ሀገራዊ ተግዳሮቶችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ያብራሩ ሲሆን÷ የኢትዮጵያ ዲጂታል ጉዞ የተገለጠበትን መንገድም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍም÷ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዟችንን ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ እንደ ሀገር ወሳኝ ርምጃዎችን ተራምደናል ብለዋል፡፡
“ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ለፈጠራ ሰዎች ድጋፍ በማስገኘት እና ለዲጂታል ጉዞ አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር በዲጂታል ኢኮኖሚ እንድንበረታ ዐቅም ሆኖናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ዛሬ ያደረግነው የመካከለኛ ዘመን ግምገማም ተግዳሮቶቻችንን ለመፈተሽ ብሎም የጉዟችንን ስኬታማ እጥፋቶች ለማክበር ዕድል ፈጥሮልናል ነው ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ የሀገር በቀል ለውጥ አጀንዳ፣ ብሔራዊ የ10 ዓመት ዕቅድ፣ የዘላቂ ልማት ግቦች ዕቅድ፣ የአፍሪካ ኅብረት አኅጉራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ማዕቀፍ ውስጥ የመነጨው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025÷ በኢትዮጵያ ፈጠራ እና የእውቀት መሠረት ያለው ኢኮኖሚ ለማደርጀት ያለመ ነው መባሉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡