አብሮ የመቆምና የመተሳሰብ ባህላችንን በማጠናከር አንድነታችንን ማጎልበት አለብን – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አብሮ የመቆምና የመተሳሰብ ባህላችንን በማጠናከር አንድነታችንን ማጎልበት አለብን ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ፤ 1 ሺህ 445ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓልን አስመልክቶ ለእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል።
እስልምና መሰረቱ ሰላም መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የኢድ አልፈጥር በዓል የሰላም፣ የአንድነትና የመተሳሰብ እንዲሁም ዕርቅ የሚወርድበት መሆኑን ገልጸዋል።
ስለሆነም የእምነቱ ተከታዮች በረመዳን ወር ሲያከናውኑት የነበረውን የእዝነት ተግባር ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።
የህዝቡን ሰላምና አንድነት በጽኑ መሰረት ላይ ማስቀመጥ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ ሕዝበ ሙስሊሙ የሃይማኖቱ ትርጉም ለሆነው ሰላም በቁርጠኝነት እንዲሰራ ጠይቀዋል።
በዚህም የጀመርነውን ጉዞ ማሳካት እንችላለን ያሉት አቶ ሽመልስ፤ መላው የክልላችን የሀይማኖት አባቶች እና የሀይማኖቱ ተከታዮች በዚህ ረገድ ብዙ ስራ ይጠበቅባችኋል ብለዋል።
ህዝበ ሙስሊሙ ኢድ አልፈጥርን ሲያከብር የተቸገሩትን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ በማመልከት፤ በዓሉ የሰላም፣ የደስታ፣ የመተሳሰብና የአንድነት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።