Fana: At a Speed of Life!

ፖለቲከኞች ለግል ጥቅማቸው ማሕበረሰብን መከፋፈል ሲፈልጉ አይሆንም ማለትን ባሕል ማድረግ ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፖለቲከኞች የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ማሕበረሰብን መከፋፈል ሲፈልጉ አይሆንም ማለትን ባሕል ማድረግ ይገባል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በገበታ ለትውልድ መርሐ ግብር የተገነባው የአርባምንጭ ኮንፈረንስ ሪዞርት በዛሬው ዕለት መርቀው ሥራ አስጀምረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት ፥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ እምቅ ሃብቶችን ለማልማት በትብብር እና በአብሮነት መንፈስ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የጋሞ እና ጎፋ ሕዝብ ከማንም በላይ በችግር እና በመከራ አብሮ የኖረ መሆኑን ጠቅሰው ÷ መተባበር እና የአንዱ ለውጥ የሌላኛውም ለውጥ መሆኑን ማመን ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የሁለቱ ወገኖች ትብብር፣ መከባበር እና መዋደድ የኢትዮጵያም ጭምር ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ጋሞ እና ጎፋ መተባበርና አብሮ መቆም ካልቻሉ ኢትዮጵያ አብራ መቆም አትችልም ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ሁሉም ብሔሮች እኩል ናቸው፤ አንዱ ከአንዱ የሚልቅ እና የሚበልጥ እንደሆነ የሚያስብ ከሆነ በሁሉም ዘርፍ ማደግ እንደማይቻል አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የስዊድን ዜጎች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ ከማንም እንደማይበልጡ እየነገሩ መሆኑን አስታውሰው÷ ልጆቹ ያዩትን ሰው ሁሉ በራሳቸው ልክ እያከበሩና እኩል እንደሆኑ እያመኑ የሚያድጉ በመሆኑ ሰላማዊ ዜጎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ይህ ባህላዊ ልምምድ እኛም ሀገር መለመድ ይኖርበታል ፤ እኛም ሀገር ሕዝቡ ሰላማዊ እና ፍቅር ቢሆንም ፖለቲከኞች ለግል ጥቅማቸው ማሕበረሰብን መከፋፈል ሲፈልጉ አይሆንም ማለትን ባሕል ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የጀመርነውና ያሳካነው ጥቂት በመሆኑ የሚጠበቅብንን ብዙ ተግባር በመደመር እና በመተባበር መንፈስ መከወን ይበልጥ ለስኬት ያበቃናል ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የአንዱ አካባቢ ልማት የሀገር የወል ልማት መሆኑን ማመን እና መቀበል ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ይጠበቃል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በአቤል ነዋይ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.