Fana: At a Speed of Life!

ኤጀንሲው ከንክኪ ነጻ የሆነ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ መሣሪያ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት አበረከተ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 04፣2012፣ (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢመደኤ/ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚያግዝ እና የጥንቃቄ እርምጃዎችን ለመተግበር የሚረዳ ከንክኪ ነጻ የሆነ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ መሣሪያ አዘጋጅቶ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በስጦታ አበረከተ፡፡

የኢመደኤ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የእጅ ንጽህና መጠበቂያ መሣሪያውን አስረክበዋል፡፡

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኤጀንሲው የተሰራውን የንፅህና መጠበቂያ መሣሪያ ከተጠቀሙ በኋላ የፈጠራ ሥራው የሚበረታታ መሆኑን ገልፀው÷ ንክኪን በማስወገድ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል የሚኖራቸውን ፋይዳ የጎላ በመሆኑ በቀጣይም መሰል የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተጠናክረው ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡

በኢመደኤ የፈጠራ ሥራው አስተባባሪ እና የማዕከሉ ኃላፊ አቶ ብሩተስፋ ሙልጌታ ÷ እንደሀገር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ኤጀንሲው ባለው አቅም የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ብሩተስፋ  አያይዘውም በተለይም ህዝብ በብዛት በሚገለገልባቸው አከባቢዎች ቴክኖሎጂውን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን  ኤጀንሲው በቀጣይም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በተለያዩ ዘርፎች ለመከላከል የሚያስችሉ የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

የፈጠራ ሥራውን በኤጀንሲው ከሰሩት ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት አቶ እንዳለ ስንታየሁ ÷ የንፅህና መጠበቂያ መሣሪያው ለአጠቃቀም ምቹ በሆነ መንገድ ሙሉ በሙሉ በኤጀንሲው ዲዛይን ተደርጎ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡

መሣሪያው በ6 ሜትር ርቀት ውስጥ ሰዎች ሲገኙ በሦስት ቋንቋዎች እጃቸውን እንዲያፀዱ ጥሪ የሚያቀርብ ሲሆን ለዚህም በዋናነት የእጅ ንፅህና መጠበቂያ ሳይኒታይዘር እና አልኮል መጠቀም እንዲቻል ተደርጎ መዘጋጀቱን አቶ እንዳለ ገልጸዋል፡፡

ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም የንፅህና መጠበቂያ መሳሪያውን ለሰላም ሚንስቴርና ለኢትዮጲያ መንገዶች ባለስልጣን ያስረከበ ሲሆን በቀጣይም ለሌሎች ሚኒስቴር መ/ቤቶች፣ ተቋማት እና ሆስፒታሎች ምርቱን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ሃላፊው መጠቆማቸውን ከኢመደኤ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.