የአውሮፕላን ማረፊያ መስፋፋትና የአዳዲስ መዳረሻዎች ግንባታ
በኢትዮጵያ የአውሮፕላን ማረፊያ መስፋፋትና የአዳዲስ መዳረሻዎች ግንባታ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ፣ ቱሪዝም እና የዓለም አቀፍ ትስስር ማደግ ከፍተኛ ፋይዳ እያበረከተ ነው።
ይህም ኢትዮጵያ ያላትን ጸጋ ለመደመር አቅም ሆኗል። በስምንት ዓመት ብቻ የተሰራውን ሥራ ስናይ የመደመር መንግሥት ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ለመረዳት ያግዘናል።
1. ሙሉ በሙሉ አዲስ የተገነቡ እና የተመረቁትን እንይ:-
ሀ. የነጌሌ ቦረና ገዳ አውሮፕላን ማረፊያ:-
በቦረና ዞን የሚገኘውን ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ልውውጥ፣ የከብት ሀብት ግብይት እና የባህል ቱሪዝምን በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል ተብሎ ይታመናል።
ለ. የጎሬ መቱ አውሮፕላን ማረፊያ:-
በታሪክ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና ያገለገለችውን ጎሬን ተደራሽ ያደረገ ሲሆን፣ አካባቢው በቡና ምርትና በተፈጥሮ ደን የታወቀ በመሆኑ ይህ አውሮፕላን ማረፊያ ለቡና ንግድና ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል።
ሐ. ሚዛን አማን አውሮፕላን ማረፊያ፦
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ለአካባቢው ማህበረሰብ የአየር ትራንስፖርት አማራጭ እየፈጠረ ነው።
መ. የጎባ (ባሌ ሮቤ) አውሮፕላን ማረፊያ፦
ከህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቱ በተጨማሪ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ የደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያን የቱሪስት መስህቦች ለማስተናገድ የተገነባ አዲስ ማረፊያ ነው።
ሠ. የነቀምቴ (ኩምሳ ሞረዳ) አውሮፕላን ማረፊያ፦
የወለጋንና የምዕራብ ኢትዮጵያን የንግድና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ ያለ።
ረ. የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ፦
የምሥራቅ ጎጃም ዞንና አካባቢውን የሕዝብና የንግድ ትስስር ለማሳደግ የተገነባ።
2. በከፍተኛ ደረጃ የታደሱ እና ደረጃቸው የፍሰት ማሳደጊያ የተደረገላቸው:-
ሀ. የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ (የመንገደኞች ተርሚናል ማስፋፊያ)፦
በዓመት የሚያስተናግደውን የመንገደኞች ቁጥር ወደ 22 ሚሊዮን ያደረሰ ዘመናዊ ማስፋፊያ ተገንብቶለታል።
ለ. የጅማ (አባ ጅፋር) አውሮፕላን ማረፊያ፦
የተርሚናል ግንባታና የበረራ ማኮብኮቢያው ደረጃው ከፍ እንዲል ተደርጎ በድጋሚ የተገነባ።
ሐ. የጅግጅጋ (ገራድ ዊልዋል) አውሮፕላን ማረፊያ፦
አዲስ ተርሚናልና ዘመናዊ አሠራር ተዘርግቶለት ደረጃው ከፍ እንዲል የተደረገ።
መ. የጎንደር (አፄ ቴዎድሮስ) እና የባሕር ዳር (አፄ ቴዎድሮስ) አውሮፕላን ማረፊያዎች፦
ለትራንስፖርት አማራጭነት እና የሰሜኑን የቱሪስት ኮሪደር ለማነቃቃት ማሻሻያ የተደረገባቸው።
ሠ. የአርባ ምንጭ አውሮፕላን ማረፊያ፦
ለቱሪዝምና ለአካባቢው ትስስር እንዲመች ተደርጎ ደረጃው የተሻሻለ።
ረ. የአሶሳ እና የጋምቤላ አውሮፕላን ማረፊያዎች፦
የደህንነትና የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶቻቸው እንዲዘምኑ ተደርገዋል።
3. በግንባታና በሂደት ላይ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች:-
የቢሾፍቱ (አቡሴራ) ሜጋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፦ በ12.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገነባውና የመጀመሪያ ምዕራፉ ሲጠናቀቅ 60 ሚሊዮን፣ በሙሉ አቅሙ ደግሞ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የሚያስተናግደው የአፍሪካ ትልቁ አየር ማረፊያ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ ግንባታው በይፋ ተጀምሯል።
4. አዳዲስ የክልል አውሮፕላን ማረፊያዎች፦
በትናንሽና መካከለኛ ከተሞች የአየር ትራንስፖርት ተደራሽነትን ለማስፋት የተጀመሩ ግንባታዎች በጥሩ አፈጻጸም ላይ ይገኛሉ።
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የግል ባለኃብቶች በትናንሽ አውሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታ ላይ እንዲሳተፉ በመንግሥት የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ የግንባታ ቦታዎችን የመለየትና ወደ ስራ ለማስገባት የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
እነዚህ መሠረተ ልማቶች ኢትዮጵያ በአፍሪካ የአቪዬሽን ዘርፍ ያላትን መሪነት ይበልጥ ለማስቀጠልና የሀገሪቱን የቱሪዝም፣ የንግድና የማህበራዊ ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።