የባለድርሻ አካላት ወኪሎች አጀንዳዎችን በየፈርጁ እያደራጁ ነው – ኮሚሽኑ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የባለድርሻ አካላት ወኪሎች አጀንዳዎችን በየፈርጁ እያደራጁ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እያስተባባረ የሚገኘው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረክ ዛሬ ለሰባተኛ ቀን እንደቀጠለ ነው።
የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች፣ ሦስቱ የመንግሥት አካላት ተወካዮች፣ የማኅበራት እና ተቋማት ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ተወካዮች በአምሥት ቡድኖች ተከፍለው ላለፉት ቀናት አጀንዳዎቻቸውን አስመዝግበዋል።
ከአምስቱ ባለድርሻ አካላት የተመረጡ ተወካዮች ደግሞ ዛሬ በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን አስቸኳይ፣ አስፈላጊ እና ወካይ በማለት በሶስት ፈርጆች እያደራጁ እንደሆነ ነው የተመላከተው፡፡
ከሰዓት በኋላ በሚኖረው ክፍለጊዜ ደግሞ በየፈርጁ የተደራጁት አጀንዳዎች ለጉባኤው ይቀርቡና ምክክር እንደሚደረግባቸው ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በዚህ ምክክር የሚደራጁት አጀንዳዎች የአዲስ አበባ ከተማ የምክክር ምዕራፍ ውጤት ይሆናሉ ብሏል ኮሚሽኑ፡፡