Fana: At a Speed of Life!

ዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር በትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍ በአጋርነት እንደሚሰራ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ ላይ ያለውን አጋርነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋገጠ፡፡

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ደዔታ በርኦ ሀሰን ከዓለም ባንክ የትራንስፖርትና ኢነርጂ ቡድን ጋር መክረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪወዎችን በስፋት ወደ አገልግሎት ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ሚኒስትር ዴዔታው በውይይቱ ላይ አስረድተዋል፡፡

በዘርፉ የ10 ዓመት የልማት ዕቅድም 148 ሺህ አውቶሞቢሎችና ከ4 ሺህ 800 በላይ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ አውቶቡሶች ወደ አገልግሎት ለማስገባት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ወደ ሀገር ለሚያስገቡና በሀገር ውስጥ ለሚገጣጥሙ አካላትም የታክስ ማበረታቻ በማድረግ እና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ በማድረግ፣ የቻርጅ መሙያ ማዕከላትን በማስፋፋት፣ በጋራዥና ጥገና ዘርፍ፣ ባለሙያዎችን በማሰልጠን በኩልም የአጋር አካላት እገዛ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡

የዓለም ባንክ የቴክኒክና ኢነርጂ ቡድኑ በበኩሉ÷ ሚኒስቴሩ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማስፋፋትና ታዳሽ የኃይል ምንጭን ጥቅም ላይ ለማዋል ለሚያደርገው ጥረት ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጧል፡፡

በተጨማሪም ተቋሙ ቅድሚያ ሰጥቶ በሚሰራባቸው ጉዳዮች እና የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን መፍታት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.