የፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የልማት ፕሮጀክት ለማካሄድ ስምምነት አደረገ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በንጹህ መጠጥ ውሃና በግብርና ዘርፍ የልማት ፕሮጀክት ለማካሄድና ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል የጋራ መግባቢያ የስምምነት ሰነድ ከክልሉ መንግስት ጋር ተፈራርሟል።
በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
አምባሳደሩ ከብኝታቸው ጎን ለጎን ወላይታ ሶዶ ተገኝተው ከርዕሰ መስተዳድሩ ተወካይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የውሃና ማዕድን ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አክሊሉ አዳኝ (ኢ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡
በዚህም የፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ በክልሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ እንዲሁም የአርሶ አደሩን የግብርና ስራዎች ውጤታማ በማድረጉ ረገድ እገዛ ማድረግ በሚችልባቸው ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል፡፡
የፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ በክልሉ በንጹህ መጠጥ ውሃና በግብርና ዘርፍ የልማት ፕሮጀክት ለማካሄድና ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል የጋራ መግባቢያ የስምምነት ሰነድ ከክልሉ መንግስት ጋር ተፈራርሟል።
ስምምነቱ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን ለማሳደግ የሚያደረገውን ጥረት እንዲሁም የአካባቢ ጥበቃና የግብርና ልማት ስራዎች ለማገዝ ያለመ መሆኑን የኤጀንሲው ተወካይ ተናግረዋል።
በስምምነቱ መሰረት ፕሮጀክቱ በወላይታ እና ጋሞ ዞኖች የተለያዩ ወረዳዎችን በንጹህ መጠጥ ውሃ እና በግብርና ልማት ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑም ተጠቁሟል።
ፕሮጀክቱ ለሚቀጥሉት 5 አመታት የሚተገበር ሲሆን÷ ከ60 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግና ከ2 ነጥብ 3 ሚሊየን ዩሮ በላይ በጀት እንደተያዘለትም ተነግሯል።
ስምምነቱን ኢንጅነር አክሊሉ አዳኝ እና የኤጀንሲው ኃላፊ ኢንጅነር አካሉ ካሣ መፈራረማቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡