የቤቶች ኮርፖሬሽን ከዓለም አቀፉ የንግድና ፋይንናስ ተቋም ጋር ተፈራረመ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የበርካታ ሀገራት ባለሃብቶች ጥምረት ከሆነው ከዓለም ዓቀፉ የንግድና የፋይንናስ ተቋም ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ስምምነቱን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል እና የዓለም አቀፉ የንግድና የፋይንናስ ተቋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኬጀ ሊ ተፈራርመዋል፡፡
ስምምነቱ በፕሮጀክት ፋይናንስ፣ በቤት ግንባታና አስተዳደር ቴክኖሎጂ አቅርቦት ላይ እንዲሁም በቬንቸር ካፒታል ኢንቨስትመንት ዙሪያ ኮርፖሬሽኑ ከተቋሙ ድጋፍ የሚያገኝበትን እድል የሚፈጥር ነው ተብሏል፡፡
አቶ ረሻድ ከማል በዚሁ ወቅት÷የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለመቅረፍና የፋይናንስ አቅሙን ለማጠናከር በርካታ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ከጠንካራ ዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ምንጮች ጋር በጋራ ለመስራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የዓለም አቀፉ የንግድና የፋይንናስ ተቋም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኬጀ ሊ በበኩላቸው÷ ኮርፖሬሽኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊለማ የሚችል ግዙፍ ሃብት ባለቤት በመሆኑ በቂ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲኖረው ተቋማቸው እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በኮርፖሬሽኑ የሥራ እንቅስቃሴ ደስተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው÷ለስምምነቱ ተግባራዊነት እንደሚሰሩ መናገራቸውን ኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
በሥነ-ሥርዓቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማና መሰረተ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እሽቱ ተሾመ (ዶ/ር ኢ/ር) ተገኝተዋል፡፡