Fana: At a Speed of Life!

ለግብርና ናሙና ቆጠራ በቴክኖሎጂ የታገዘው የሰው ሃይል ምልመላ ውጤታማ መሆኑ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሀገር አቀፍ የግብርና ናሙና ቆጠራ በቴክኖሎጂ ታግዞ የተደረገው የሰው ሃይል ምልመላ ሒደት ውጤታማ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በ2017 በጀት ዓመት ለሚያካሂደው የግብርና ናሙና ቆጠራ የሰው ሃይል ምልመላ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በለማው የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት ለማከናወን የጋራ መግባቢያ ስምምነት ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱ ይታወሳል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚልና የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌን (ዶ/ር) ጨምሮ የሁለቱም ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት የምልመላ ሒደቱ ተገምግሟል፡፡

በመድረኩ 43 ሺህ 500 የመስክ መረጃ ሰብሳቢዎችን ለመቅጠር በወጣው ማስታወቂያ መሰረት በ5 የሥራ ቀናት ውስጥ ብቻ ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች ለሥራው ማመልከታቸው ተጠቁሟል፡፡

በዚህም በሁሉም ክልሎች ባሉ ቀበሌዎች ደረጃ ታሳቢ ባደረገ የምዝገባ ስርዓት መስፈርቱን የሚያሟሉ 73 ሺህ የሚሆኑ ዕጩዎች አጭር የጽሑፍ መልዕክት ተልኮላቸው ፈተናውን በኦንላይን እንዲወስዱ እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡

ይህም የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓት ለውጭ ሀገር ብቻ ሳይሆን ለሀገር ውስጥ ሥራ ስምሪቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አንደሚያሳይ ተጠቅሷል፡፡

የለማው ስርዓት በዲጂታል ስርዓት ከአድሎ የፀዳ፣ ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋ እና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመረውን ሀገራዊ ጥረት በእጅጉ የሚያግዝ እንደሆነም መገለጹን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.