የተለያየ መጠን ያለው ጤፍ፣ ስንዴና ሽንኩርት ለአዲስ አበባ ገበያ መቅረቡ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ እየተደረገ ያለው ክትትልና ቁጥጥር ተጠናክሮ መቀጠሉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በዚህ መሰረትም በዛሬው ዕለት 1 ሺህ 552 ያለአግባብ ዋጋ የጨመሩ እና 49 ሕገ ወጥ ክምችት የፈፀሙ የንግድ ተቋማት መታሸጋቸው ተገልጿል፡፡
ሶስት የንግድ ተቋማት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረጋቸው ንግድ ፍቃዳቸው የታገደ ሲሆን÷ ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ያደረገ 1 ነጋዴ ደግሞ መታሰሩ ተጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል በመዲናዋ የሰብል ምርቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬ አቅርቦት እጥረት እንዳያጋጥም የከተማ አስተዳደሩ ከኦሮሚያ ክልል ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር የተለያዩ ምርቶች ለገበያ መቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡
በዚህም 133 ሺህ 485 ኩንታል ጤፍ፣ 54 ሺህ 683 ኩንታል የስንዴ ዱቄት፣116 ሺህ 194 ኩንታል ስንዴ፣ 64 ሺህ 102 ኩንታል ገብስ፣ 49 ሺህ 162 ኩንታል በቆሎ እንዲሁም 38 ሺህ 844 ኩንታል ሽንኩርትና 17 ሺህ 476 ኩንታል ቲማቲም ለአዲስ አበባ ገበያ መቅረቡ ተጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል በፈፀሙት ሕገ ወጥ የንግድ ተግባር ድርጆቶቻቸው ከታሸጉባቸው 28 ሺህ 338 ውስጥ 26 ሺህ185 የንግድ ድርጅቶች የውል ስምምነት እየፈጸሙ እሸጋው የተነሳላቸው መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
እስካሁን ከታሰሩት 778 ነጋዴዎች ውስጥ 385 ነጋዴዎች ከእስር መፈታታቸውንም ብሄራዊ የንግድ ተቋማት ፀረ ሕገ ወጥ ንግድና ገበያ ቁጥጥር ኮሚቴ አስታውቋል፡፡