Fana: At a Speed of Life!

የፋይናንስ ዘርፉ ጤናማ፣ የተረጋጋና ደህንነቱ የተጠበቀ ሆኖ እየተንቀሳቀሰ ነው – ብሔራዊ ባንክ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ያለው የፋይናንስ ዘርፍ ጤናማ፣ የተረጋጋና ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑ ተገምግሟል አለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፡፡

ባንኩ የፋይናንስ ስርዓቱን ደህንነት ለማረጋገጥ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት ሦስተኛውን የፋይናንስ ደህንነት ግምግማ ሪፖርት ይፋ ያደረገ ሲሆን፥ ሪፖርቱ ከሐምሌ 2016 እስከ ሰኔ 2017 ዓ.ም ያለውን ጊዜ የሚሸፍን መሆኑን አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ፋይናንስ ስርዓት በውጫዊና ውስጣዊ ጫናዎች፣ በቀጣናዊ ውጥረትና ሌሎች ተግዳሮቶች ውስጥ ማለፉን የጠቀሰው ሪፖርቱ፥ ኢኮኖሚው እነዚህን ዓለም አቀፍ ጫናዎች ተቋቁሞ መሻሻል ማሳየቱን ጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2017 በጀት ዓመት በማክሮ ኢኮኖሚ መመዘኛዎች መሰረት እድገት ማስመዝገቡን፣ የተረጋጋ የፋይናንስ ስርዓት መፈጠሩንና የዋጋ ንረት መቀነሱን ገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የታየው የኢኮኖሚ እድገት የገንዘብ ፖሊሲን ውጤታማነት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት አዎንታዊ አስተዋፅኦ ማበርከቱንም ነው ባንኩ የገለጸው፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ተጋላጭነት መቀነሱን፣ የበጀት አፈጻጸሞች መሻሻላቸውን እንዲሁም የሀገር ውስጥ ዕዳ መቀነስ ማሳየቱን አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ የባንከ፣ የማይክሮ ፋይናንስ፣ የካፒታል ገበያ እና የማህበራዊ ዋስትና ዘርፎች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ በመምጣቱ የግብይት መጠን በእጥፍ ማደግ 18 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር መድረሱንም ገልጿል።

የዲጂታል ፋይናንስ ዕድገት የፋይናንስ ተደራሽነትን ቢያሰፋም ከሳይበር ጥቃትና ከማጭበርበር ጋር የተያያዙ ስጋቶችን ለመከላከል የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማትን ማጠናከርና የሰው ኃይል አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ ብሔራዊ ባንክ በሪፖርቱ አስገንዝቧል።

በአጠቃላይ የፋይናንስ ስርዓቱ ጤናማ፣ የተረጋጋ፣ ትርፋማ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ሆኖ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ባንኩ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.