Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌት የሚያዘገይ ምንም ነገር የለም- ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህዳሴ ግድብን የውሃ ሙሌት የሚያዘገይ ምንም ነገር እንደሌለ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለፁ።

ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አጠቃላይ ሁኔታ እና ወቅታዊ ጉዳዮችን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

ሚኒስተሩ በመግለጫቸው እንዳሉት ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ የተነሱት ግርግሮች ከህዳሴው ግድብ ጋር የተያያዘ ሴራ እንዳለው አመላካች ነገሮች አሉት።

የአርቲስቱ ግድያ በተፈፀመበት እለት የህዳሴ ግድብ ጉዳይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ከሚታይበት 30 ደቂቃ ቀደም ብሎ ነበር።

በመሆኑም በእለቱ የተፈፀመው ወንጀል ጉዳዩን በቀጥታ በሚከታተሉት የመንግስት ባለስልጣናት ላይ የራሱ የሆነ ጫና ፈጥሮ ነበር ብለዋል።

ይሁን እንጂ የግድቡን የግንባታ ሂደትና የውሃ ሙሌት “ሊያስትጓጉል የሚችል ነገር የለም፤ አይኖርምም” ሲሉ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት የግድቡን ሁለት ተርባይኖች ስራ ለማስጀመር የሚያስችል የውሃ ሙሌት ለመጀመር ዝግጅቱ ተጠናቋል ብለዋል።

“ኢትዮጵያ በጥቂቶች ሴራ የምትፈርስ የእምቧይ ካብ አይደለችም” ያሉት ሚኒስትሩ የግድቡም የውሃ ሙሌትም በተያዘለት ፕሮግራም ይከናወናል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ለችግሮች ትብብርና በጋራ መቆምን እንጂ ለአፍራሾች በራቸውን ክፍት የማያደርጉ ህዝቦች መሆናቸውንም በቅጡ መረዳት ይገባል ብለዋል።

የህዝቡን አንድነት፣ በጋራ መቆምና ልማቶችን ለማደናቀፍ እየተሸረቡ ያሉ ሴራዎች መኖራቸውን እንገነዘባለን ያሉት ዶክተር ስለሺ ከልማታችን ሊያደናቅፈን የሚችል ችግር አይኖርም ብለዋል።።

የኢትዮጵያ ህዝብም “የመከፋፈያ እና ግጭት ተውኔት” የሚያመጡ ሃይሎችን በመጋፈጥ የህዳሴውን ግድብ ጨምሮ ለሌሎች ፕሮጀክቶችም እውን መሆን እንዲያተኩር ጠይቀዋል።

የህዳሴ ግድብን በሚመለከት ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በሁለት ሳምንት ውስጥ ድርድሩን እንዲጨርሱ ተወስኖ ነበር።

ይሁን እንጂ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ላይ በተፈፀመው ግድያ እና ይህንን ተከትሎ በነበረው አለመረጋጋት ድርድሩ ባለፈው ሰኞ ሳይጀመር ቀርቷል።

ድርድሩ ቀደም ብሎ ተይዞለት በነበረው እለት ባይካሄድም ከአርብ እለት ጀምሮ በመካሄድ ላይ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ በድርድሩ ላይ 11 ታዛቢዎች እየተሳተፉ ሲሆን፥ በእስካሁኑ የድርድር ሂደት ስምምነት የተደረሰባቸውና ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች ተለይተዋል።

የሶስቱ ተደራዳሪ ሀገራት ቀጣይ የድርድር ሂደትም በህጋዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር መሆኑን ገልጸዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.