ወጣቱ ላልተገባ የጥፋት ድርጊት ከሚገፋፉት ሀይሎች ራሱን ሊጠብቅ እንደሚገባ የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አሳሰበ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) +ወጣቱ ላልተገባ የጥፋት ድርጊት ከሚገፋፉት ሀይሎች ራሱን ሊጠብቅ እንደሚገባ የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ፊልሰን አብዱልሂ አሳሰቡ።
የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ህልፈት የሀገር ጉዳት እና የህዝቡም ህመም መሆኑ ቢታወቅም፤ ሀዘንና ህመማችንን መግለጽ ያለብን ለሌላ ቀውስና ጉዳት ራሳችንን አጋልጠን መሆን የለበትም ብለዋል ሚኒስትሯ ዛሬ በሰጡት መግለጫ።
ሀዘናቸውን በሰላማዊ መንገድ ወጥተው ለአርቲስቱ ያላቸውን ክብር፣ ፍቅርና ቁጭት በመግለጽ ድርጊቱን ወጥተው ያወገዙ፣ የተቃወሙ ወጣቶች ይህ ስራቸው ለአርቲስቱም ክብር ለህዝቡም ሰላም፣ ለሀገሪቱም ተስፋ ለአጥፊዎችም ትምህርት ለጠላቶችም ሽንፈት ነው ብለዋል።
በህዝቦች መካከል ፍቅርን እንጂ ጥላቻን መንዛትና ማቃቃር እንኳንስ ለአንድ ሀገር ህዝቦች ለጎረቤታሞችም የማያዛልቅ በመሆኑ ወጣቱ ለሀገራዊ አንድነት እና ልማት በጊዜያዊ ጥቅም እንዳይታለል ሲሉ ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል።
የሚዲያ ተቋማትም ለሀገሪቱና ለህዝቦቿ የሚጠቅሙ እንዲሁም የህዝቡን አንድነት የሚያስጠብቁ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ በማድረስ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በዘቢብ ተክላይ
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።