ከንቲባ አዳነች አቤቤ የከተማዋ ነዋሪዎች አራዳ ፓርክን ለወራት በነፃ እንዲጎብኙ ጋበዙ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለነዋሪዎች ያማረ እና በቂ የመዝናኛ ቦታዎችን ለማቅረብ ካለማናቸው ቦታዎች አንዱ አራዳ ፓርክ ነው አሉ የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ ለከተማችን ነዋሪዎች ምቾት፣ ለከተማ ውበት ብሎም ለቱሪስት ፍሰት ትልቅ ፋይዳ ያለው እንዲሁም ያማረ እና በቂ የመዝናኛ ቦታዎችን ለማቅረብ ካለማናቸው ቦታዎች አንዱ አራዳ ፓርክ ነው ብለዋል።
በውቧ አራዳ ፓርክ ውስጥ የታሪክ መመልከቻ ጋላሪ፣ የንግድ ቦታዎች – ከሱፐር ማርኬት፣ ባንኮች እስከ የተለያዩ እቃዎች መሸጫ ሱቆች፣ ካፍቴሪያዎች፣ አዳራሾች፣ ሆቴሎች፣ ፀጉር ቤቶች፣ የስፓርት መስሪያ ጅምናዚየሞች፣ የሳይክል ውድድር ማድረጊያዎች፣ የመሮጫ ትራክ፣ ፋውንቴይንና የልጆች መጫወቻዎች ወዘት ከበቂ የመኪና ማቆሚያ ጋር ሁሉም በአንድ ቦታ ላይ ተዘጋጅተው ያገኛሉም ነው ያሉት።
ይህ ለከተማችን አዲስ ገፅታን የፈጠረው የውቧ አራዳ ፓርክ ለመላው የከተማችን ነዋሪዎች ለቀጣይ ወራቶች በነፃ እንድትጎበኙ ከፍት የተደረገ በመሆኑ መጥታችሁ ከግብይት ማዕከላቱ እንድትሸምቱ እንዲሁም በመዝናኛ ማዕከላቱ እንድትዝናኑ ተጋብዛችኋል ሲሉም ገልጸዋል።