የኢሳ ማሕበረሰብ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት ተመዘገበ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢሳ ማሕበረሰብ ባሕላዊ የዳኝነት ሥርዓት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት ተመዝግቧል፡፡
19ኛው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ጥበቃ የበይነ መንግሥታት ኮሚቴ ስብሰባ በፓራጓይ አሶንሲዮን እየተካሄደ ነው፡፡
ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ በጋራ ያቀረቡት “ሄር ኢሴ”፡ የሶማሌ ኢሣ ማኅበረሰብ ያልተጻፈ ባሕላዊ ሕግ በመልቲናሽናል ሰነድነት በሰው ልጆች ወካይ ዓለም አቀፍ የማይዳሰስ ቅርስነት ተመዝግቧል።
በስብሰባውም ላይ ኢትዮጵያን በመወከል የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኢብራሂም ኦስማን ፋራሕ በመገኘት ንግግር አድርገዋል።
ዩኔስኮ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍም÷ የኢሳ ማህበረሰብ ባሕላዊ የዳኝነት ሥርዓት በማይዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ መካተቱን አስታውቋል፡፡