በትግራይ ክልል የወባ ስርጭትን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ታሕሣሥ 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)በትግራይ ክልል የተከሰተውን የወባ ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፌደራል መንግስት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን በትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ጤና ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች መከላከል ባለሙያ ዕቑባይ ገብረእግዚአብሔር ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ በክልሉ በአሁኑ ወቅት የወባ በሽታ ያልተከሰተበት አካባቢ እንደሌለ ጠቁመዋል።
በዚህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በያዝነው የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በበሽታው የተያዘው የሰው ቁጥር በእጥፍ መጨመሩን ተናግረዋል።
ከባለፈው ዓመት ጥር 1 ቀን 2016 ጀምሮ እስከዚህ ወር ድረስ 362 ሺህ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን እና ከእነዚህም ውስጥ 20 ሰዎች በበሽታው ምክንያት ህይወታቸውን ማጣታቸውን ባለሙያው አብራርተዋል።
ባለሙያው፥ በክልሉ በነበረው ጦርነት ምክንያት የህብረተሰቡ ግንዛቤ መቀዛቀዝ፣ የመቆጣጠርና መከላከል ስራ መቀነስ፣ ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች መኖር፣ በቂ የመድኃኒት አቅርቦት አለመኖር ለበሽታው መስፋፋት እንደምክንያት አንስተዋል።
በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠርም የክልሉ የጤና ቢሮ፣ የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ተቋማት በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የጤና ሚኒስቴር፥ በክልሉ ያለውን የወባ በሽታ ስርጭትን ለመቀነስ በ16 ወረዳዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለ5 ወራት ያህል የክትትልና ድጋፍ ስራ መስራቱንም ገልጿል።
ይሁን እንጂ ስርጭቱ ከተጠቀሱት ወረዳዎች በተጨማሪ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም በመስፋፋቱ ምክንያት፥ ይህን ለመከላከል የሚያስችል 88 አባላት ያቀፈ 22 የህክምና ቡድን መቋቋሙን አብራርቷል።
የጤና ሚኒስቴር በተለይ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ በክልሉ እያደረገ ያለው ድጋፍ የላቀ መሆኑን የገለጹት አቶ ዕቑባይ በ2017 ዓ.ም በ6 ወረዳዎች የጸረ-ወባ ኬሚካል ርጭት ማካሄዱን ጠቅሰዋል።