የአየር አምቡላንስ አገልግሎት በኢትዮጵያ ለማስጀመር የሰነድ ዝግጅት እየተደረገ ነው ተባለ
አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአየር አምቡላንስ አገልግሎት በኢትዮጵያ ለማስጀመር የሰነድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን በጤና ሚኒስቴር የሜዲካል አገልግሎት መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ኢሉባቦር ቡኖ ገለጹ፡፡
ዶክተር ኢሉባቦር ቡኖ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት ፥ አገልግሎቱ በግጭት፣ በእሳት አደጋ፣ የተሟላ አገልግሎት ከሚሰጡ ጤና ተቋማት በርቀት ላይ ያሉ አልያም በሌሎች ምክንያቶች ከፍተኛ የድንገተኛ ህክምና ቢያስፈልግ ታካሚዎችን በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም ለማድረስ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም አስፈላጊ የህክምና ግብዓቶችን እና ባለሙያዎችን በፍጥነት ከተፈለገበት ቦታ ለማድረስ ያግዛልም ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የአየር አምቡላንስ ዜጎች ድንገተኛ ከባድ ህክምና ቢያጋጥማቸው እና ወደ ውጭ ሀገር ሄደው እንዲታከሙ ቢያስፈልግ በፍጥነት ለማድረስና የሜድካል ቱሪዝምን ለማሳለጥ ይረዳል ብለዋል ፡፡
እንዲሁም በመደበኛ አውሮፕላን መንቀሳቀስ የማይችል ግለሰብ በዚሁ የአየር አምቡላንስ ማሽን ላይ የጤና ባለሙያዎች የህክምና እርዳታ እየሰጡት ወደ ውጭ ሀገር ሄዶ መታከም ይችላልም ብለዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ