Fana: At a Speed of Life!

የብሔራዊነት ገዥ ትርክትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር ይሠራል- የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔራዊነት ገዥ ትርክት የመፍጠር የሕዝቦች ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር የተጀመሩ ሥራዎችን በትጋት እንደሚያስቀጥሉ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ገለጹ፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ከጥር 23 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም ባካሄደው ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ባወጣው የአቋም መግለጫ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር እና የሀገረ መንግሥት ግንባታ እንዲሳካ ነጣጣይ ትርክቶች ተሸንፈው አስተሣሣሪ ትርክቶች የበላይነት ማግኘት እንዳለባቸው ገልጿል፡፡

የብሔራዊነት ገዥ ትርክት በልሂቃን እና በሕዝቡ ዘንድ እንዲሠርጽና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር በስፋት እንደሚሠራም ነው በአቋም መግለጫው የተመላከተው፡፡

የብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና በፓርቲው የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ መሐመድ ሁሴን÷ በኢትዮጵያ የተፈጠረው አዲስ የፖለቲካ ባህል ነጣጣይ ትርክትን በማስቀረት አሰባሳቢ ትርክት እንዲፈጠር ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያዊያንን አብሮነት በማጠናከር ረገድ የብሔራዊነት ገዥ ትርክት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም አንስተዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባል እና በፓርቲው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢሳቅ አብዱልቃድር በበኩላቸው÷ ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ ለማረጋገጥ በትጋት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በቀጣይም የብሔራዊነት ገዥ ትርክት ለማስረፅና በሕዝቦች መካከል ትሥሥርና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጎልበት ብልፅግና ፓርቲ በመሪነት እንደሚሠራ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያዊያንን የሚያሰባስቡና ለጋራ ግብ የሚያነሳሱ ስራዎች መከናወናቸውን የገለጹት ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባል እና በፓርቲው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝብች ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ፍቅሬ አማን ናቸው።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.