Fana: At a Speed of Life!

የተባበሩት መንግሥታት የዘላቂ ልማት መፍትሔ ጥምረት የአፍሪካ ቢሮ በአዲስ አበባ ተከፈተ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተባበሩት መንግስታት የዘላቂ ልማት መፍትሔ ጥምረት የአፍሪካ ቢሮ በኢትዮጵያ መከፈቱ በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች ላይ ያላትን የነቃ ተሳትፎ የሚያሳይ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የዘላቂ ልማት መፍትሔ ጥምረት የአፍሪካ ቢሮውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መክፈቱን ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡

በመርሐ ግብሩ አቶ አህመድ ሽዴን ጨምሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፣ የተመድ የዘላቂ ልማት መፍትሔ ጥምረት ፕሬዚዳንት  ጄፍሪ ሳክስ (ፕ/ር) እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

አቶ አህመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሁሉን አቀፍ ሪፎርም አድርጋለች፡፡

የኢትዮጵያ የ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ዘላቂ ልማትን የሚያረጋግጥ መዳረሻውን ብልጽግና ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች አካታች ሪፎርም መደረጉን ገልጸው፥ ኢትዮጵያ የዘላቂ የልማት ግቦችን በማሳካት የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገቧን ጠቅሰዋል፡፡

በምሥራቅ አፍሪካ ትልቅ ህዝብና ኢኮኖሚ የላት ሀገር መሆኗን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፥ በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ምስረታና አበርክቶ የጎላ ሚና እንዳላትም ገልጸዋል፡፡

ጥምረቱ የአፍሪካ ቢሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መከፈትም ኢትዮጵያ በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁነቶች ያላትን የነቃ ተሳትፎ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እድገት ማስመዝገብ በሚያስችል ቁመና ላይ የተመሰረተ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ÷ ግቡን ለማሳካት የተለያዩ የፖሊሲ ርምጃዎች ተወስደዋል ብለዋል፡፡

የውስጥ ገቢ አሰባሰብን ማዘመን፣ ኢንቨስትመንትን ማሳደግ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ማሻሻል ትኩረት የተደረገባቸው እንደሆኑም ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.