Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በቱሪዝም ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት የጎብኚዎች ቁጥር እያደገ መጥቷል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል በቱሪዝም ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት የጎብኚዎች ቁጥር እያደገ መጥቷል አለ የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አየለ አናውጤ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የክልሉን እምቅ የቱሪዝም ሃብት አልምቶ በመጠቀም ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ ነው።
በመደመር መንግሥት ቱሪዝም ከዋና የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ አንዱ ሆኖ መወሰዱና ትኩረት መሰጠቱ ዘላቂነት ያለው እድገት እንዲመዘገብ አስችሏል ነው ያሉት፡፡
በዚህም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በክልሉ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን ማልማት መቻሉን ገልጸው፤ ነባር ቅርሶችን በመጠገንና በመንከባከብ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡
ከፋሲል አብያተ መንግስታት እድሳት በተጨማሪ የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት፣ የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ግንባታና መሰል ተግባራት የክልሉ ቱሪዝም በፍጥነት እንዲነቃቃ እያደረገ መሆኑንም በማሳያነት አንስተዋል፡፡
በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው በባህር ዳር የሚገኘው የደጅ አዝማች በላይ ዘለቀ አውሮፕላን ማሪፊያ አዲሱ ተርሚናል ለክልሉ ቱሪስት ፍሰት ማደግ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
በደብረ ማርቆስ ደግሞ የንጉስ ተክለሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያ ወደ አገልግሎት መግባት አካባቢውን ለቱሩስቶች ይበልጥ የተመቸ ያደርገዋል ብለዋል።
በተጨማሪም የጣና ነሽ ቁጥር 2 ጨምሮ ሌሎች ዘመናዊና ፈጣን ጀልባዎች ቁጥር ማደግ የባህር ላይ ቱሪዝም እንቅስቃሴን እያጠናከረ መሆኑን አብራርተዋል።
እነዚህ የባህር፣ የምድር እና የአየር ላይ የትራንስፖርት አማራጮች መዘርጋታቸው የክልሉን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ይበልጥ በማነቃቃት በኩል የራሳቸውን አስተዋጾ እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።
የትራንስፖርት አማራጮች መዘርጋታቸው ባህር ዳርን ከጎርጎራ፣ ከጎንደር እና ከሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጋር በማስተሳሰር ቱሪስቶች በአንድ ጉዞ ሁሉንም እንዲመለከቱ እድል ፈጥሯል ነው ያሉት።
በዘርፉ በተከናወኑ ተግባራት የሃገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሃገራት ጎብኚዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን አንስተው፤ በ2018 በጀት ዓመት ብቻ 54 ሺህ የውጭ ሃገራት፤ 18 ሚሊየን የሃገር ውስጥ ቱሪስቶች የመስህብ ሃብቶችን ጎብኝተዋል ብለዋል።
በክልሉ የቱሪስት መስህብ ሃብቶችን የማስተዋወቅ፣ መዳረሻ ስፍራዎችን የማልማትና መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራዎች በቀጣይም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመትም ከ21 ሚሊየን በላይ የሃገር ውስጥ እና ከ101 ሺህ በላይ የውጭ ሃገራት ቱሪስቶች የክልሉን የመስህብ ሃብቶች እንዲጎበኙ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.