ከእናትና አባት ዐርበኞች የተማርነው ራስን ሠውቶ ሀገርን ማኖር ነው – ም/ጠ/ሚ ተመስገን
አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከእናትና አባት ዐርበኞች የተማርነው ራስን ሰውቶ ሀገርን ማኖር እንጂ ሀገርን ሠውቶ ራስን ማኖር አይደለም ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው እለት የታሰበውን የየካቲት 12 ሰማዕታት ቀን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያን ያቆዩት በመሥዋዕትነት፣ ለዛውም ከውስጥና ከውጭ ባንዳ ጋር እየታገሉ መሆኑን አንስተዋል።
በአምስቱ ዓመት የፋሺስት ጣሊያን ወረራ ጊዜ ዐርበኞች ለነጻነት እና ለሉዓላዊነት ሲታገሉ ባንዳዎች ደግሞ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ከጠላት ጋር ተባብረው ሀገራቸውን ሲወጉ እና ሲያስወጉ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ባንዶች ይሄንን የሚያደርጉት ሕዝባቸውን ሽጠው የልብስ እላቂ እና የወርቅ ድቃቂ ለማግኘት መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የሀገር ጠላት በመጨረሻ እነርሱንም እንደማያተርፋቸው ያውቃሉ ብለዋል፡፡
ዛሬም ለግል ጥቅማቸው ከምንጊዜም የሀገር ጠላት ጋር አብረው የገዛ ሀገራቸውን የሚወጉ እና ሆድ ከሀገር፣ ሥልጣን ከሕዝብ የሚበልጥባቸው ባንዳዎች መኖራቸውን አመላክተዋል፡፡
አስደሳቹ ነገር ግን ዛሬ ከባንዳዎቹ የዐርበኞቹ ቁጥር ይበልጣል፤ ኢትዮጵያ ፈተናውን ሁሉ በማሸነፍ በሁለንተናዊ ብልፅግና ላይ መራመዷ ለዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከእናትና አባት ዐርበኞች የተማርነው ራስን ሠውቶ ሀገርን ማኖር እንጂ ሀገርን ሠውቶ ራስን ማኖር አይደለም፣ በዛሬው ቀን የተሰው ሰማዕታትንም አንረሳም ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፡፡