ሚኒስቴሩ በሕገ-ወጥ ነዳጅ ንግድ የተሰማሩ አካላትን እንደማይታገስ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በሕገ-ወጥ ተግባር የተሰማሩ የነዳጅ ኩባንያዎችና በሥራቸው የሚገኙ ማደያዎች በፍጥነት ወደ ሕጋዊነት እንዲገቡ አሳሰበ፡፡
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ከነዳጅ ኩባንያ ባለቤቶችና ሃላፊዎች ጋር በነዳጅ አቅርቦትና ሥርጭት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም በነዳጅ ኩባንያዎች፣ በነዳጅ ማደያዎችና እና በየደረጃው በሚገኙ የመንግስት አደረጃጀቶች በኩል ያሉ ውስንነቶች ዙሪያ መክረዋል፡፡
መንግስት ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ ብዙ ቢሊየን መዋዕለ ንዋይ እየደጎመ ነዳጅን አቅርቧል ያሉት ሚኒስትሩ÷ በዚህ መልኩ የገባን ነዳጅ በግብይት ሰንሰለቱ ውስጥ ያሉ ተዋንያን እንዳሻቸው ሊያደርጉት አይገባም ብለዋል፡፡
በውይይቱ በሕገ-ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ የነዳጅ ኩባንያዎች እና በሥራቸው የሚገኙ ማደያዎች በፍጥነት ወደ ሕጋዊነት እንዲገቡ አሳስበዋል፡፡
ነዳጅ በሕገ-ወጥ መንገድ በችርቻሮ የሚሰራጭበትን ሁኔታ ለማስቆም የተጀመሩ ርምጃዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ሰው ሰራሽ የገበያ እጥረትን በመፍጠር ያልተገባ ትርፍ ለማጋበስ የሚደረጉ ጥረቶችን እንደማይታገስም አስታውቀው፤ ከዚህ በኋላ ሕገ-ወጥነትን ለመከላከል ጨክነን ተገቢውን ርምጃ እንወስዳለን ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡