ቴክኖሎጂን የችግር መፍቻ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ – ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቴክኖሎጂን ለህዝባችን ችግር መፍቻ እና የእድገታችን ማፍጠኛ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ገለጹ።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ለሀገረ መንግስት ግንባታ መሰረት የሚጥሉ ነፃ፣ ገለልተኛና ብቃት ያላቸውን ተቋማት የመገንባት ሂደት ዘርፈ ብዙ ውጤቶች ማስመዝገባቸውንም ተናግረዋል።
በተቋማት ግንባታ ላይ በተለይ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ከተሰሩ ሥራዎች መካከል ነባር ተቋሞችን አሰራርና አገልግሎታቸውን ማዘመን እንዲሁም አዳዲስ ተቋማት መገንባትና በሰለጠነ የሰው ሃይል የማጠናከር ሥራ በትኩረት በመስራት ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
ከጉባኤ እስከ ጉባኤ ባለው ጊዜ ውስጥ አዲስ ከተቋቋሙት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት÷ ለህዝብና ሀገር የሚጠቅሙ በርካታ ሥራዎች መሥራቱንም አመልክተዋል።
ትላልቅ ሀገራት እየተወዳደሩበት ያሉ የወደፊት ነዳጅ እየተባለ የሚነገርለት የዳታ ቋት በመገንባት አሁን ላይ 30 ተቋማት ውስጥ በሥራ ላይ መዋሉን ገልጸው÷ የዳታ ቋቱ ለመጪው ትውልድ የምናወርሰው፤ አሁን ያለው ትውልድ ተጠቅሞ ችግርን የሚፈታበት ነው ብለዋል።
የሀገሪቱ ቋንቋዎች የማሽን ቋንቋ ባለመሆናቸው ለጥናትና ምርምር ዝግጁ ያልሆኑበት ሂደት ስለነበረ በዚህ ረገድ በተሰሩ ሥራዎች በአሁን ወቅት አምስት ቋንቋዎችን የማሽን ቋንቋ ማድረግ መቻሉን መግለፃቸውን የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል።