የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት አፈፃፀም 48 ነጥብ 5 በመቶ ደረሰ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ሃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክትን እስከ ሐምሌ ወር ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጅ ቴዎድሮስ ጋሻው እንዳሉት÷ ጣቢያው 14 ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጭ መስመሮች እና እያንዳንዳቸው ባለ 63 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያላቸው አራት ትራንስፎርመሮች እንዲኖሩት ተደርጎ እየተገነባ ነው፡፡
የማከፋፈያ ጣቢያውን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች ለማስቀመጥ የሚያግዙ ከ290 በላይ የመሠረት ቁፋሮና የኮንክሪት ሙሌት እንዲሁም የአራት ትራንስፎርመሮች ማስቀመጫ ግንባታዎች መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈጻፀም 48 ነጥብ 5 በመቶ መድረሱን ጠቁመው፤ ቀሪ የመንገድ፣ የመቆጣጠሪያ ክፍል ግንባታ እና የፍሳሽ ማስወገጃ እንዲሁም የኤሌክትሮ ሚካኒካል ሥራዎችን የማካካሻ እቅድ በማውጣት እስከ ሐምሌ ወር ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ባለስልጣን ለሚያስገነባው ስማርት ሲቲ በተለያዩ ምዕራፎች እንዲቀርብለት ከሚፈልገው 575 ሜጋ ቮልት አምፔር ኃይል ውስጥ ፕሮጀክቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ 252 ሜጋ ቮልት አምፔር ኃይል ለማቅረብ እንደሚያስችል መግለፃቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ አመላክቷል።
የማከፋፈያ ጣቢያውን ጨምሮ 2 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ርዝመት ላለው የማስተላለፊያ መስመር የግንባታ ሥራ ወጪ በገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ባለስልጣን መሸፈኑ ተገልጿል።
ፕሮጀክቱ 181 ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድሎች መፍጠሩ ተነግሯል።