Fana: At a Speed of Life!

የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ የሚያስችል የጋራ መግባቢያ ሰነድ ጸደቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ19ኛው የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽነሮች ጉባዔ ሀገርን በጋራ ለማፅናት እና የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያስችል የጋራ መግባቢያ ሰነድ ጸድቋል።

የጋራ መግባቢያ ሰነዱ ዓላማ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ተጠያቂነት እና ዘላቂነት ያለው ቅንጅት በመፍጠር የፀጥታ ችግሮችን በጋራ በመፍታት ሕብረተሰቡ በፖሊስ ላይ ያለውን እምነት የበለጠ ማሳደግ መሆኑ ተገልጿል።

ወንጀልና የሽብር ተግባር ለመፈፀም ለሚያስቡም ሆነ ፈጽመው ለመሰወርና ለሚፈልጉ መደበቂያ ለማሳጣት ተቀናጅቶ እና ተማምኖ ለመስራት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተመላክቷል።

እንዲሁም ወንጀለኛ ብሄር፣ ዘር፣ ሃይማኖት እና ድንበር የሌለው በመሆኑ ሁሉም የፖሊስ ተቋማት ወንጀል ፈፅመው ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል የሚሸሸጉ ተጠርጣሪዎችን ይዞ ለመመርመርና ለሕግ ለማቅረብ የሚደረገው ጥረት አጠናክሮ ለማስቀጠል ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው19ኛው የፖሊስ ኮሚሽነሮች ጉባዔ ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት በዛሬው ዕለት መጠናቀቁን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.