Fana: At a Speed of Life!

ዓድዋ የነጭና ጥቁር ሕዝቦችን የሚዛን ልዩነት የቀየረ ድል ነው -ርዕሳነ መስተዳድሮች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ እና የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ ለ129ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ባስተላለፉት መልዕክት÷የዓድዋ ድል በኢትዮጵያ እውነተኛ ማንነት፣ በአባቶቻችን የደም ቀለም እና በጀግኖቻችን አጥንት የተጻፈ ድል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዓድዋ የውስጥና የውጭ ገጽታ ተግዳሮቶችን ያጠፋ፣ የጥቁርና የነጭ ልዩነቶችን ሚዛን የቀየረ ታላቅ ድል እና የጋራ ትርክታችን መሠረት ነው ሲሉም አውስተዋል፡፡

ዓድዋ የጋራ ታሪክን የገነባ፣ ወንድማማችነትን ያጠናከረ እና ሀገራዊ አንድነትን ያከበረ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ዓድዋ ከልዩነት ይልቅ አንድነትን፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን፣ ከጥፋት ይልቅ ግንባታን፣ ከመገለል ይልቅ አብሮነትን ያስተማረ በመስዋዕትነት የተገኘ ድል መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳደር ሙሰጠፌ መሃመድ በበኩላቸው÷ዓድዋ ከ129 ዓመታት በፊት ጀግኖች የሀገራችን ሉዓላዊነት ከማስከበር አልፈው የጥቁር ሕዝቦችን አንገት ቀና ማድረግ የቻሉበት ታሪካዊ ቀን ነው ብለዋል፡፡

ይህንን ታሪክ በልማት በመድገም ኢትዮጵያ የምታልመውን የብልጽግና ራዕይ ማሳካት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡

መንግስት የዓድዋ ድል ታሪኮችን በማደስና በማሰባሰብ ሀገራችን የአፍሪካዊያንን የነፃነት ተምሳሌት መሆኗን ዳግም ከማረጋገጡ ባሻገር ዓድዋን ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ ቀን ማድረግ መቻሉን አመላክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.