ተረጂነትን ለማስቀረት የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት አስመዝግበዋል – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ፣ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ከማሳደግና ተረጂነትን ለማስቀረት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገቡ ነው ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም የሁለተኛ ቀን ግምገማ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡
በግምገማው የኑሮ ውድነትን ከማረጋጋት፣ ክህሎት መር የስራ ዕድል ፈጠራ ከማሳደግ እንዲሁም ከተረጂነት ለመላቀቅ እየተከናወኑ በሚገኙ ስራዎች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፡፡
በግምገማ በመድረኩ አቶ አደም ፋራህ እንዳሉት÷ የኑሮ ውድነት በመቆጣጠር፣ የምርት አቅርቦትን በማሳደግና ገበያን በማረጋጋት እንዲሁም አምራችና ሸማችን በማገናኘት ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
በሀገር ደረጃ ተቀርጸው ወደ ሥራ የገቡ የተለያዩ ኢኒሼቲቮች ምርትና ምርታማነትን ከመጨመር አኳያ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ከክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ አኳያም ተጨባጭ የሚባሉ ለውጦች መታየታቸውን ገልጸው÷ለበርካታ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድሎች መፈጠራቸውን ጠቁመዋል፡፡