ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በሁሉም ዘርፎች ሰፊ የልማት ሥራ ላይ ትገኛለች – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በግብርና ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዘርፎች ሰፊ ልማት ላይ ትገኛለች አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኦቢኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎች እና ትግሎች፣ የኢትዮጵያ ታሪክ እና የኦሮሞ ሕዝብ አበርክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን ዘርፈ ብዙ ለውጥ መካድ አይቻልም፤ ይሁን እንጂ የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል ሰፊ ሥራ እና ድካም ይጠይቃል ብለዋል፡፡
በተጨባጭ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ነገር በብዛት ታይቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ለአብነትም በኦሮሚያ ክልል የግብርና ምርት ከ168 ሚሊየን ኩንታል ወደ 510 ሚሊየን ኩንታል የታየው እድገት ትልቅና አበረታች ውጤት መሆኑን አንስተዋል፡፡
የሀብት ማደግ የሕዝብን ተጠቃሚነት በቀጥታ እንደሚያሳድግ ጠቅሰው ÷ በተለይም በከተሞች ልማት በኩል ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል።
ለአብነትም በቢሾፍቱ፣ አዳማ፣ ጅማ፣ ሮቤ እና በሌሎች ከተሞች የታየው እንቅስቃሴ የዚሁ ትልቅ ለውጥ ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል።
የተመዘገቡትን ድሎች መጠበቅ፣ ማስፋፋትና የእነዚህን ድሎች እጥረት እየሞሉ መሄድ የትውልድ ሥራ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ ሀገርን በመገንባት ሒደት ደሙን፣ አጥንቱን እና ላቡን በማፍሰስ አስፈላጊውን መስዋዕትነት መክፈሉንም አውስተዋል፡፡