ሠራዊታችን ከወገንተኝነት የፀዳ የሠላም ኃይል ነው- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሠራዊታችን ከፖለቲካ፣ ከዘርና ከሐይማኖት ወገንተኝነት የፀዳ የሠላም ኃይል ነው ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ፡፡
የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ለሦስት ዓመታት በዲግሪ መርሐ-ግብር ያሰለጠናቸውን የ70ኛ ዙር ቃኘው ኮርስ ዕጩ መኮንን ሰልጣኞች አስመርቋል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን የለውጥ ጉዞ ለማደናቀፍ የውስጥ እና የውጭ ኃይሎች ያለ እረፍት እየሠሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በመሆኑም ተመራቂ ሰልጣኞች በአመራር ጥበብና ብቃት በመመርኮዝ እነዚህን የጥፋት ኃይሎች መታገል እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
የዛሬ ጀማሪ የመኮነንነት ማዕረግ ለነገ ጄነራልነት መነሻ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፤ ተመራቂዎች እችላለሁ በሚል መንፈስ መልካም አጋጣሚዎችን በመጠቀም ራሳቸውን ማብቃትና ለተልዕኮ መዘጋጀት አለባችሁ ብለዋል፡፡
በስልጠና ቆይታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች የዋንጫ፣ የወርቅ ፣ የብርና የነሃስ ሜዳሊያ ሽልማት መበርከቱን ከመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡