በ10 ዓመት የልማት እቅዱ በባቡር ትራንስፖርት ዘርፍ ኢትዮጵያን ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ለማድረግ መታቀዱ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የትራንስፖርት ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት የሆኑት የማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን፣ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን እና የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር አክስዮን ማህበር የ10 ዓመት የልማት እቅዳቸውን አቅርበው ውይይት ተደረጎበታል፡፡
በውይይቱም የማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ ደረቅ ወደብን ማልማት ለሃገር ውስጥ የግል ዘርፍ የተተወ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ባለሃብቶችም ክፍት መሆኑን ተናግረዋል።
የሎጂስቲክስ ስርዓቱን በማዘመን አለም አቀፍ የሎጂስቲክስ አፈጻጸም ኢንዴክሱን አሁን ካለበት 126ኛ ደረጃ ወደ 40ኛ ደረጃ ማሳደግን ርዕዩ ማድሩጉንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር አክስዮን ማህበር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሰረካ በበኩላቸው በ10 ዓመት የልማት እቅዱ በባቡር ትራንስፖርት ዘርፍ ኢትዮጵያን ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ለማድረግ መታቀዱን ነው የተናገሩት፡፡
አደረጃጀቱን በማሻሻል እና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተገልጋዩን ህብረተሰብ ለቅሬታ የሚዳርገውን አገልሎት አሰጣጥ ለማሻሻል በ10 ዓመት እቅዱ መቀመጡን ደግሞ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይረክተር አቶ አብዲሳ ያደታ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡