Fana: At a Speed of Life!

የከርሰ ምድር ውሃ ያለበትን ደረጃ የሚያጠና ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 26፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዴንማርክ መንግስት ከሀዋሳ እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የከርሰ ምድር ውሃ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ እና ውሃው ያለበትን ደረጃ የሚያጠና ፕሮጀክት ይፋ አድርገዋል።

የኢትዮ-ኔቸር ፕሮጀክት የሀዋሳ ማዕከል አስተባባሪ ሙሉጌታ ዳዲ (ዶ/ር) ፕሮጀክቱ ለ5 ዓመት እንደሚቆይ ገልጸው÷ በዚህ ጊዜ በሀዋሳ ሃይቅ ዙርያ ያሉ ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራል ብለዋል።

በውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈፃሚ ደበበ ዳፋርሶ÷ በኢትዮጵያ በውሃ ሀብት አጠቃቀም ላይ ባለው ችግር ሀብቱን በተገቢው መጠቀም አለመቻሏን አንስተዋል።

ችግሩንም ከከፍተኛ ትምህርት ተባባሪ አካላት ጋር በመሆን የማስተካከያ ርምጃ በመውሰድ ሀገሪቱ ያላትን የውሃ ሀብት በመለየት ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል ብለዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት በሚገባ ማስተዳደር ባለመቻሉ መጠቀም በምትችለው ደረጃ አለመጠቀሟን ገልጸዋል።

ከግለሰብ እስከ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ያለው ተገቢ ያልሆነ የውሃ አጠቃቀም ችግር የከርሰ ምድርና የገፀ-ምድር ውሃ እንዲባክንና ለብክለት እንዲጋለጥ አድርጓልም ነው ያሉት።

ለአምስት ዓመታት በዴንማርክ መንግስት ድጋፍ ተግባራዊ የሚደረገው ፕሮጀክቱ በውሃ ሀብት አስተዳደር ላይ የነበሩ ችግሮችን ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ምላሽ ለመስጠት ያስችላል ነው ያሉት።

በታመነ አረጋ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.