Fana: At a Speed of Life!

የካይሮ የሴራ ቀለበት፤ ከካርቱም እስከ አስመራ

በአፍሪካ ቀንድ ላይ የሚነፍሰው የጦርነትና የአለመረጋጋት ንፋስ ድንገት የመጣ አይደለም።
ቀጣናው በጦርነት እየተናጠ፤ በችጋርና ችግር አለንጋ እየተገረፈ የኖረው፤ እጣ ፈንታው ሆኖ አይደለም። በስውር ሴራ፤ በረቀቀ ስልት፤ የአንዲትን ሀገር መረን የለሽ ፍላጎት እንዲያስፈጽም ተፈርዶበት እንጂ።
ይህችን ሀገር ፍለጋ ብዙም መንከራተት አያሻም። ሀገሪቱ ባሕሩም፤ ውሃውም ለኔ ጥቅም ብቻ ይዋል የሚል ስግብግብ አቋም ያላት ግብጽ ናት።
ለዚህ የኖረ እውነት፤ ብዙ መረጃ ለማቅረብ የግብጽን የግልጽ እና ሰውር እጆች መከተል በቂ ነው። ከሁለቱ ሱዳኖች እስከ ኤርትራ፤ ቀጥሎም ወደ ሶማሊያ እናቅና፤ በዚያ ግብጽን እናገኛታለን። በዚያውም ግብጽ እኩይ ፍላጎቷን ለማሳካት በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ላይ የዘረጋችውን የሴራ ድር እና ታሪካዊ ሐቆች በጥቂቱ እንመልከት።
ግብጽ ሱዳንን እንደራሷ የደህንነት ቅጥያ (Buffer Zone) እና በናይል ጉዳይ ላይ የድጋፍ ድምፅ ማግኛ አድርጋ ነው የምታያት። የታሪክና የውጭ ጉዳይ ተንታኞች (ለምሳሌ አሌክስ ዲዋል (Alex de Waal) በሱዳን ጉዳይ ላይ ባደረጋቸው ጥናቶች) እንዳረጋገጠው፤ ግብጽ በሱዳን ጠንካራና ሉዓላዊ መንግሥት እንዲኖር አትፈልግም።
የዘወትር የካይሮ ጸሎትና ትጋቷ፤ ሱዳን እስከ ዓለም ፍፃሜ በሚንበረከክ ወታደራዊ አመራር እየማቀቅች እንድትኖር ማድረግ ነው። አሁን ባለው እና ከሶስኛ አመቱን እየደፈነ ባለው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የግብፅ ጦር የሱዳንን ጦር ኃይል (SAF) በድብቅ በድሮንና በስለላ መረጃ በመደገፍ ጦርነቱ እንዲራዘምና ሱዳን እንድትዳከም አድርጓል።
የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ለግብጽ ሲሳይ ነው። ደካማ ሱዳን ብሄራዊ ጥቅሟን አሳልፋ ሰጥታ፤ የግብጽ ድብቅ ፍላጎት ማስፈፀሚያ ሆናለች። ይህ እንዲቀጥል የእርስ በርስ ጦርነቱ መቆም የለበትም።
እናም ግብጽ በጦርነት እሳቱ ላይ ቤንዚን ታርከፈክፋለች። ይህ እቶን እሳትም እንደ ሀገር ሱዳንና ህዝቦቿን እያቀጠለ፤ የወላፈኑ ሙቀትም በአፍሪካ ቀንድ የሚሰማ ሆኗል። የካይሮ ፍላጎት ይህንን እሳት በመላው አፍሪካ ቀንድ ማዳረስ ነው።
ግብጽ በደቡብ ሱዳን አማፂያንን በመደገፍ እና ከጁባ መንግሥት ጋር ወታደራዊ ስምምነት ለመፈረም ስትጥር መቆየቷን The EastAfrican እና ሌሎች ቀጣናዊ የሚዲያ ምንጮች በተደጋጋሚ ዘግበውታል። በተለይም በደቡብ ሱዳን “ፓጋክ” በተሰኘ አካባቢ የጦር ሰፈር የመገንባት ግቧን ለማሳካት ብዙ ጥራለች።
የደቡብ ሱዳንን መንግሥት የፍላጎቷ ተገዥ እንዲሁን የደቡብ ሱዳን አማጽያንን እስከመደገፍ ተጉዛለች። የኋላ ኋላ የጁባ መንግሥት የሉዓላዊነት ስጋት ስላሳደረበትና የጎረቤት ሀገራትን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ እንዲከሽፍና የግብጽ ኃይሎች እንዲወጡ ተደርጓል።
ከዚህ ርምጃ በኋላ ግብጽ ካራ መሳሏን ቀጥላለች። ደቡብ ሱዳንን ልክ እንደ ሱዳን ሁሉ ወደለየለት የእርስ በርስ ግጭት በመክተት፤ ተንበርካኪ መንግሥት የመፍጠር አምሮቷ እስካሁን አልቆረጠላትም። የአፈሪካ ቀንድም ለማተራመስ የተዘረጋው የግብጽ እጅ እስኪቆረጥ ድረስ ጁባ ሌላዋ ኢላማ ናት።
የኤርትራ የውጭ ፖሊሲ ጠባይ ተጠቅሞ የአፈሪካ ቀንድን ማተራመስ ሌላው የግብጽ ስልት ነው። እንደሚታወቀው የኤርትራ መንግሥት ከጎረቤቶቹ ጋር ያለው ግንኙነት በግጭት ላይ የተመሰረተ ለመሆኑን እማኝ አያሻም።
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ የገንዘብና የደህንነት ዋስትና እስካገኙ ድረስ የግብጽ በቀጣናው ለሚኖራት የውክልና ጦርነት ግዛቷንና የሰው ኃይሏን በኪራይ መልክ እንደምታቀርብ የተለያዩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባለሙያዎች ቡድን ሪፖርቶች አረጋግጠዋል።
ኤርትራ የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ የተለኮሰው እሳት ፍም አዟሪ ናት። በደረሰችበት ሁሉ ፍሙን በመጣል ቀጣናውን ለማጫረስ የኤርትራ መንግሥት ጥሩ የግብጽ ተላላኪ ነው።
ኤርትራ የሶማሊያን መንግሥት ለማዳከም ለአልሸባብ የጦር መሣሪያና የገንዘብ ድጋፍ ታደርግ እንደነበር የተባበሩት መንግሥታት ማዕቀብ የጣለባት ታሪካዊ ማስረጃ ነው። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ግብጽ ይህንን የኤርትራን እረፍት አልባ ጠባይ በመጠቀም፣ የኤርትራንና የሶማሊያን የጋራ ጸረ ኢትዮጵያ ግንባር በማስተባበር ላይ ትገኛለች።
ይሄ ሁሉ የግብጽ ሴራ መዳረሻ የቀይ ባሕር እና የባብል አል መንደብ የትርምስ ማእከል አድርጎ ብቸኛ ተፈላጊ ሀገር ሆኖ መቅረብ ነው። የግብፅ የውጭ ምንዛሪና የኢኮኖሚ ሕልውና የተመሰረተው በሱዌዝ ቦይ ላይ ነው።
ይህ ቦይ ሥራ እንዲሰራ ደግሞ የባብል አል-መንደብ ወሽመጥና የቀይ ባሕር ቀጣና ሁልጊዜም በወታደራዊ ውጥረት ውስጥ መቆየት አለበት።
ቀጣናው ሰላም ሆኖ ሀገራዊ ኃይሎች (እንደ ኢትዮጵያ) የራሳቸውን የባሕር ኃይልና የኢኮኖሚ የበላይነት ከገነቡ የካይሮ የሞኖፖሊ ተፅዕኖ ያበቃለታል። ስለዚህ ካይሮ የቀይ ባሕር ተሻጋሪ ሀገራት ሁሌም በውስጥ ትርምስ ውስጥ እንዲኖሩ ስልታዊ ሴራዎችን ስትጎነጉን ኖራለች።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.