የኢትዮ ኮደሮች ስልጠና ያጠናቀቁ ከ270 ሺህ በላይ ወጣቶች የምስክር ወረቀት ወስደዋል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ5 ሚሊየን የኢትዮጵያ ኮደሮች ፕሮግራም እስከ አሁን ከ270 ሺህ የሚልቁ ወጣቶች ሥልጠናቸውን በማጠናቀቅ የምስክር ወረቀት መውሰዳቸው ተገለጸ፡፡
በመላ ሀገሪቱ ባለፉት 10 ወራት ከ800 ሺህ በላይ ወጣቶች ተመዝግበው ስልጠናቸውን በመከታተል ላይ እንደሚገኙ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አማካሪ አብዮት ባዩ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
ከእነዚህ መካከል ከ200 ሺህ የሚልቁት በመሠረታዊ ፕሮግራሚንግ፣ ከ235 ሺህ በላይ በዳታ ሣይንስ፣ ከ220 ሺህ በላይ በአንድሮይድ ፕሮግራሚንግ እንዲሁም ከ125 ሺህ በላይ ደግሞ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እየሰለጠኑ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል ከ270 ሺህ በላይ ወጣቶች ስልጠናቸውን በማጠናቀቅ የምስክር ወረቀት መውሰዳቸውን ገልጸዋል፡፡
የ5 ሚሊየን የኢትዮጵያ ኮደሮች ፕሮግራም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን መሠረት በማድረግ መቀረጹንም አስረድተዋል፡፡
ይህም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የለሙትን መተግበሪያዎች ተጠቅሞ እሴት የሚፈጥር እና በሂደትም መተግበሪያዎችን የሚያለማ እና የዲጂታል መሠረተ ልማቶችን የሚያሥተዳድር የሰው ኃይል እንዲኖረን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው