የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በሁሉም ዘርፍ የተገኙ ስኬቶችን አጉልቶ ለማሳየት የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
“ድኅረ እውነት ዘመንን በእውነት እና ዕውቀት” በሚል መሪ ሐሳብ ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጠ ነው።
ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ እውነተኛ መረጃ ለሕብረተሰቡ በማድረስ የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያሳዩና የጠላቶችን ሴራ የሚያጋልጡ የኮሙኒኬሽን ሥራዎች ላይ ማተኮር ይገባል ብለዋል፡፡
ዘርፉ ገዢ ትርክትን ለሕብረተሰቡ ለማስረጽ ዋና መሳሪያ መሆኑን ገልፀው፤ ለአመራሩና ለኮሙኒኬሽን ባለሙያው ግንዛቤ ማሳደግ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በብልጽግና ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኢሳቅ አብዱልቃድር በበኩላቸው፤ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ የሕዝቦችን ትስስር፣ የጋራ ትርክት ግንባታን የሚያጠናክር እና አንድነትን የሚያጎለብት መረጃ በመስጠት በኩል ጠንክሮ እንዲሠራ አስገንዝበዋል፡፡