Fana: At a Speed of Life!

ቼልሲ ከማንቼስተር ዩናይትድ….

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ37ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ቼልሲ በሜዳው ስታምፎርድ ብሪጅ ምሽት 4 ሠዓት ከ15 ላይ ማንቼስተር ዩናይትድን ያስተናግዳል።

በ63 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ለሚቀጥለው የውድድር ዘመን የሻምፒየንስ ሊግ ተሳትፎ ቦታን ለማግኘት በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ለመቆየት ይፋለማል።

በዚህ የውድድር ዓመት በሊጉ 17 ጨዋታዎችን የተሸነፈው ማንቼስተር ዩናይትድ ይህ ቁጥር ከፍ እንዳይል ብርቱ ፉክክር እንደሚያርግ ይጠበቃል።

በአሰልጣኝ ሩበን አሞሪም የሚመራው ማንቼስተር ዩናይትድ በ39 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሁለቱ ቡድኖች እርስበርስ ባደረጓቸው አምስት ያለፉት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ማንቼስተር ዩናይትድ በሁለቱ ሲያሸንፍ ቼልሲ በአንዱ ድል አድርጎ በሁለቱ አቻ ተለያይተዋል።

በዚህ የውድድር ዘመን በኦልድትራፎርድ ባደረጉት የመጀመሪያ ዙር የሊጉ ጨዋታ አንድ አቻ መለያየታቸው አይዘነጋም።

በሌላ የሊጉ ጨዋታ አስቶንቪላ ምሽት 3 ሠዓት ከ 30 ላይ በሜዳው ቪላ ፓርክ ቶተንሃም ሆትስፐርን ያስተናግዳል።

ባለሜዳው ቡድን አስቶንቪላ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ቦታን ለማግኘት በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ለመቆየት ወሳኙን ሦስት ነጥብ ለማሳካት ወደ ሜዳ  ይገባል።

ደካማ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው ቶተንሃም ሆትስፐር በክሪስታል ፓላስ ከደረሰበት ሽንፈት ለማገገም እና ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

አስቶንቪላ በ63 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ፤ ቶተንሃም ሆትስፐር በ38 ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.