ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የሰው ሰራሽ አስተውሎት ልማት ዘርፍ በአስደናቂ መንገድ ላይ ትገኛለች – የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የሰው ሰራሽ አስተውሎት ልማት ዘርፍ በአስደናቂ መንገድ ላይ መሆኗን የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር ሰልማ ማሊካ ሃዳዲ ገለጹ።
ሁለተኛ ቀኑን በያዘው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክስፖ 2025 “አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ለአፍሪካ ብልጽግና እና ትብብር” በሚል መሪ ሃሳብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር ሰልማ ማሊካ ሃዳዲ እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤክፖ ጠቃሚና ወቅቱን የዋጀ ነው።
በአፍሪካ አካታችና ዘላቂ የሰው ሰራሽ አስተውሎት በመገንባት ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ነው ብለዋል።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት በጂኦ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አንዱ የለውጥ ኃይል እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው÷ የሀገራት የብሔራዊ ጥቅም ማስከበሪያ፣ ኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ማረጋገጫ እና የደህንነት ዋስትና የትኩረት ማዕከል ሆኗል ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ስትራቴጂ አጀንዳ 2063ን ማሳካት የሚያስችል ልማት ላይ መሆኗን እና ይህም ሀገር በቀል ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በማልማት ከሕብረቱ አጀንዳ ግብ ጋር የተጣጣመ ውጤት እያስመዘገበች መሆኗን ያሳያል ብለዋል።
ሀገር በቀል የሰው ሰራሽ አስተውሎት ልማት ለአፍሪካ እድገት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው÷ኢትዮጵያ በዘርፉ የብዝሃ ባህል፣ ቋንቋና የብዝሃ ዘርፍ ልማትን በማካተት በአስደናቂ መንገድ ላይ መሆኗን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ሰው ሰራሽ አስተውሎት በፈጠራ፣ በትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና፣ ፋይናንስ፣ በደህንነትና ብሔራዊ ጥቅምን በማስከበር የጎላ አበርክቶ እንዳለው ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን በማቋቋም ሰው ሰራሽ አስተውሎት በልማት ላይ ጉልህ ሚና እንዲጫወት መደረጉን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ በ2030 የአፍሪካ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የልህቀት ማዕከል የመሆን ራዕይ መሰነቋን ጠቁመው÷ ለሌሎች ሀገሮች ልምዷን ለማካፈል ዝግጁ እንደሆነች መናገራቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።