የአማራ ክልል ልማት፣ ሰላምና መረጋጋት ዘላቂና አስተማማኝ በሆነ መልኩ እየተገነባ ነው
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የክልሉ ልማት፣ ሰላምና መረጋጋት ዘላቂና አስተማማኝ በሆነ መልኩ እየተገነባ መሆኑን የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
በአማራ ክልል በልማት እንቅስቃሴው፣ በአሁናዊ የሰላም ሁኔታና ቀጣይ ትኩረት በሚደረግባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት በኮምቦልቻ ከተማ ተካሂዷል።
የሰሜን ምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌትናል ጀነራል አሰፋ ቸኮልን ጨምሮ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ የጸጥታ አባላትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች በመድረኩ ተሳትፈዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ የሰላምና የልማት ጉዳይ ሁሉንም የሚመለከት የጋራ አጀንዳ መሆኑን አንስተዋል።
በየደረጃው ያለው አመራር፣ የጸጥታ ሃይሉ፣ ህብረተሰቡና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት በቁጭት በመስራታቸው ውጤት መምጣቱንም ተናግረዋል።
በዚሀም የክልሉ ልማት፣ ሰላምና መረጋጋት ዘላቂና አስተማማኝ በሆነ መልኩ እየተገነባ ነው ብለዋል።
የሰላምና የልማት ጸር በመሆን ሲንቀሳቀስ የነበረው ጽንፈኛ ቡድን በተወሰደበት ጠንካራ እርምጃ እየከሰመ መሆኑን ገልጸው÷ በርካቶችም የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል እጃቸውን በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በመሆኑም የተገኘውን ሰላም በማጽናት የልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አንስተው፥ ህብረተሰቡና በየደረጃው ያለው አመራር ለበለጠ ስኬት ይበልጥ ተባብረው እንዲሰሩ አስገንዝበዋል።
የዛሬው የውይይት መድረክ ዋነኛ ዓላማም ጽንፈኛውን ሃይል እስከ መጨረሻው በመታገል ሰላምን የማጽናትና ልማትን የማስቀጠል መሆኑን ማንሳታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።