በአማራ ክልል ለአረንጓዴ አሻራ 201 ሺህ ሄክታር መሬት ተለይቷል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል በመጪው ክረምት ለሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር እስካሁን 201 ሺህ ሄክታር መሬት መለየቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ ለቀጣዩ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡
በዚህ መሰረት በክልል ደረጃ በ69 ሺህ የችግኝ ጣቢያዎች 1 ነጥብ 6 ቢሊየን በላይ ችግኝ ለማፍላት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ እስካሁን 1 ነጥብ 46 ቢሊየን ችግኝ ለቆጠራ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከችግኝ ማፍላት ጎን ለጎንም የመትከያ ቦታ የመለየት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑ ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
ለመርሐ ግብሩ 207 ሺህ ሔክታር የመትከያ መሬት ለማዘጋጀት ታቅዶ እስካሁን 201 ሺህ ሄክታር ተለይቶ ዝግጁ መደረጉን አንስተዋል፡፡
በሌላ በኩል እስካሁን ሕብረተሰቡን በማሳተፍ ለችግኝ መትከያ የሚውል 120 ሚሊየን በላይ ጉድጓድ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡
ለመትከያ አገልግሎት ለሚውሉ ቦታዎች የካርታ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ