Fana: At a Speed of Life!

በሀገር በቀል መፍትሄዎች ችግሮችን ለመፍታት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ችግሮችን በሀገር በቀል መፍትሄዎች ለመፍታት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

በምግብ ራስን ለመቻል የተካሄዱ ጥረቶች እና የተገኙ ልምዶች የሚገመግምበት መድረክ በጅማ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

አቶ አደም ፋራህ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ ያላትን መሬት እና የሰው ኃይል አጣምራ አለመጠቀሟ ለበርካታ ዓመታት ለተረጂነት ዳርጓት ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት ሀገር በቀል ሪፎርሞችን እና ማሻሻያዎችን በመተግበር በምግብ ራስን ለመቻል እየተሰራ ያለው ሥራ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ ባለፈም የምግብ ሥርዓት ሽግግር እሳቤ ኢትዮጵያ እየገጠማት ያለውን ውስብስብ ችግር ለመፍታት ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቁመው÷ የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎትን በራስ አቅም ለመሸፈን በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ ሰውን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎች መተግበር የላቀ ውጤት ማስመዝገብ ማስቻሉን አንስተዋል።

በሌማት ትሩፋት እየተተገበረ ባለው ሥራ 26 ሚሊየን የነበረውን የአንድ ቀን ጫጩት ሥርጭት ባለፉት 10 ወራት ወደ 100 ሚሊየን ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።

በአሮሚያ ክልል በም/ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ÷ በክልሉ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራ በ102 ወረዳዎች ውስጥ ሲተገበር እንደነበር ገልጸው፤ በ2018 ዓ.ም 57 ወረዳዎች እንደሚካተቱ አመልክተዋል።

በተጨማሪም በራስ አቅም ራስን ለመቻል እየተሰራ ያለው ሥራ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን ነው የተናገሩት፡፡

በሙክታር ጠሃ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.