Fana: At a Speed of Life!

ማንቼስተር ሲቲ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ቦታን ለማግኘት….

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ37ኛ ሣምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ማንቼስተር ሲቲ በሜዳው ኢትሀድ ምሽት 4 ሠዓት ላይ ቦርንማውዝን ያስተናግዳል።

የውድድር ዓመቱን ያለ ምንም ዋንጫ ያጠናቀቀው ማንቼስተር ሲቲ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን በሻምፒየንስ ሊግ የሚያሳትፈውን ቦታ ለማግኘት እየተፋለመ ይገኛል።

በአሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ የሚመራው ሲቲ በ65 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን፤ ጨዋታውን ካሸነፈ ነጥቡን 68 በማድረስ ደረጃውን በማሻሻል 3ኛ ላይ መቀመጥ ይችላል።

በ53 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ተጋጣሚው ቦርንማውዝ ድል ከቀናው ነጥቡን ወደ 56 ከፍ በማድረግ በደረጃ ሠንጠረዡ 8ኛ ላይ ይቀመጣል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሁሉም ውድድር እርስበርስ ባደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ማንቼስተር ሲቲ አራቱን ሲያሸንፍ፤ ቦርንማውዝ በአንዱ ድል አድርጓል።

በሣምንቱ መጨረሻ በኤፍ ኤ ካፕ የፍፃሜ ጨዋታ በክሪስታል ፓላስ ተሸንፎ ዋንጫውን ያጣው ሲቲ፤ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እና የአውሮፓ መድረክ ተሳታፊ የሚያደርገውን ነጥብ ለማግኘት ይፋለማል።

በዚህ የውድድር ዓመት በሊጉ ባደረጉት የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ቦርንማውዝ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል።

በሌላ ጨዋታ በተመሳሳይ ምሽት 4 ሠዓት ላይ ክሪስታል ፓላስ በሜዳው ዎልቭስን ያስተናግዳል።

ክሪስታል ፓላስ በ49 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ዎልቭስ በበኩሉ በ41 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ባለሜዳው ቡድን ፓላስ በሣምንቱ መጨረሻ ማንቼስተር ሲቲን በማሸነፍ የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫን ማንሳቱ ይታወሳል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች እርስበርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ክሪስታል ፓላስ ሦስቱን ሲያሸንፍ፤ ዎልቭስ በአንዱ ድል አድርጎ በቀሪው አንድ ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

ፓላስ በሣምንቱ መጨረሻ ሲቲን በኤፍ ኤ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ ያሸንፍ እንጂ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በአንዱ ብቻ ነበር፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.