Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የስደተኞችን እንክብካቤ ለማሳደግ ያለመ አካታች ስትራቴጂ በቅርቡ ልትጀምር ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የስደተኞችን እንክብካቤ ለማሳደግ ወደ ልማት ተኮር ስትራቴጂ ለመሸጋገር ያለመ አካታች ስትራቴጂ በቅርቡ እንደምትጀምር ገለጸች።

ኢጋድ በሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ለሚከሰቱ መፈናቀሎች እና በስደት ላይ ያተኮረ የሁለት ቀናት የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ማካሄድ ጀምሯል።

የኢጋድ ምክትል ዋና ጸሐፊ መሀመድ አብዲ ዋሬ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ የሚፈናቀሉ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ከሁሉን አቀፍ ልማት እንቅስቃሴ ጋር ማስተሳሰር ያስፈልጋል።

በሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ለሚከሰቱ መፈናቀሎች መፍትሄ ለመስጠት የባለድርሻ አካላት ቅንጅት መጠናከር እንዳለበትም አመልክተዋል።

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አማካሪ ዘውዱ በዳዳ፤ ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት እና ከተባበሩት መንግሥታት ጋር በመሆን ባህላዊ የካምፕ አቀራረብ ሞዴል ራዕይ መቅረጿን ተናግረዋል።

ይህም በቀጣይ ኢትዮጵያ ስደተኞችን እንክብካቤ ለማሳደግ ወደ ልማት ተኮር ስትራቴጂ ለመሸጋገር ያለመ አካታች ስትራቴጂ በቅርቡ እንደሚጀመር ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ረዳት ተወካይ ዴቪድ ካርፕ በበኩላቸው፤ በቀጣናው የሚደረገው የስደተኞች ምላሽ በለውጥ ላይ እንደሚገኝ እና ይህም አስደናቂ አመራር መኖሩን የሚያሳይ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.