Fana: At a Speed of Life!

ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለውን ትስስር ያጠናከረው አረንጓዴ አሻራ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጋራ ልማትና ትስስርን ማጠናከሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

መርሐ ግብሩ በዲፕሎማሲው መስክ በዓለም አቀፍ መድረክ ዕውቅና እና ተቀባይነት ማግኘቱን በሚኒስቴሩ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሽብሩ ማሞ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጥ እንደመሆኑ የጋራ ተጠቃሚነትና ቀጣናዊ ትስስርን የበለጠ ለማጠናከር በመሰረተ ልማት፣ በንግድ፣ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ በትብብር እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር አብሮ የመልማት፣ የመበልጸግ፣ የተፈጥሮ ሃብትን በዘላቂነት በመጠበቅ በፍትሐዊነት የመጠቀም አቋሟን ያጠናከረችበትና በተሞክሮነት የተወሰደ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖችም መርሐ ግብሩን ለማስፋትና ለማስተዋወቅ በትኩረት እየሠሩ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለጎረቤቶቿ ችግኝ በመስጠት፣ በመትከልና ልምድ በማካፈል ትስስርን ለማጠናከር እየሠራች መሆኗንም አስታውቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.