በጾም ወቅት ይቅርታና መረዳዳት ሊጠናከሩ ይገባል – የሃይማኖት አባቶች
አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጾም ወቅት ይቅርታና መረዳዳት ይበልጥ ሊጠናከሩ ይገባል አሉ የሃይማኖት አባቶች፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ የዐብይ ጾም በትናንትናው ዕለት ተጀምሯል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የስብከተ ወንጌልና ሐዋሪያዊ ተልዕኮ መምሪያ ኃላፊ መላከ ሰላም ቀሲስ ዳዊት ያሬድ ዐብይ ጾም ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ አርዓያ ለመሆን የጾመ በመሆኑ የእርሱ ተከታዮች ሃይማኖታዊ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ መጾም አለብን ብለዋል፡፡
የሰው ልጅ የእግዚአብሔር ስለመሆኑ መታወቂያው ካለው ላይ ለሌላው ሲያካፍል ነው ያሉት መላከ ሰላም ቀሲስ ዳዊት÷ ለሌሎች ማካፈል በፍቅርና በትህትና መከናወን እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ምክትል ጠቅላይ ጸሐፊ እና የሐዋሪያዊ ስራ ዋና ኃላፊ አባ አብርሃም ገ/ማርያም በበኩላቸው እንዳሉት÷ ዐብይ ጾም ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ የከፈለውን መስዋዕትነት በጾም፣ በጸሎት እና በመልካም ስራ ራሳችንን የምንፈትሽበት ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ለሚሰቅሉት ሁሉ ይቅርታና ምህረትን እንደማለደ ሁሉ እኛም ከጎናችን ላሉ ወንድሞቻችን ይቅርታና መልካም ነገር ማድረግ አለብን ብለዋል፡፡
በዚህ የጾም ወቅት ከውጫዊ ነገሮች ይልቅ ልባዊ ለውጥ ያስፈልጋል በማለት ገልጸው÷ ይህም አብሮ መኖር፣ ለሌሎች መልካም ማሰብና ከግለኝነት ይልቅ ማህበራዊነት ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡
የሐይማኖቱ ተከታዮች ወቅቱ የይቅርታና ምህረት፣ በጎነት እና መረዳዳት እንዲሁም ለሀገር ሰላም መጸለይ የሚገባ በመሆኑ ይንህኑ እንዲያደርጉ የሃይማኖት አባቶቹ አሳስበዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ