በዓሣ ማስገር ለተደራጁ ወገኖች የሥራ ዕድል መፍጠር የጀመረው የሕዳሴ ግድብ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዓሣ ማስገር ዘርፍ የተደራጁ ሁሉም ማኅበራት ወደ ሥራ እንዲገቡ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
በግድቡ ዓሣ ለማስገር በ74 ማኅበራት ከተደራጁ 704 ወንዶች እና 145 ሴቶች መካከል በሥራ ላይ ያሉት በ30 ማኅበራት የታቀፉ 400 ወንዶች እና 107 ሴቶች መሆናቸውን የቢሮው ኃላፊ ባበክር ኸሊፋ ተናግረዋል፡፡
የተወሰኑት ወደ ሥራ ያልገቡት ከዘመናዊ የዓሣ ማስገሪያ ግብዓት እጥረት ጋር በተያያዘ መሆኑን ጠቁመው፤ ለአብነትም የጀልባ፣ መረብ፣ የዓሣ ማጓጓዣ ፍሪጅ መኪና፣ የማቆያ ፍሪጅ እና የፋይናንስ አቅርቦትን ጠቅሰዋል፡፡
ግድቡ በዓመት እስከ 15 ሺህ ቶን ዓሣ የማምረት አቅም እንዳለው በጥናት መረጋገጡን አቶ ባበክር ኸሊፋ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡
ሁሉም ማኅበራት ወደ ሥራ ባለመግባታቸው ምክንያት ባለፉት 10 ወራት ማምረት የሚጠበቀውን ያህል ማምረት እንዳልተቻለ ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ከማስገሪያ ግብዓቶች ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ በመሆኑ ሁሉንም ማኅበራት ወደ ሥራ ማስገባትና የዓሣ ምርትን ማሳደግ ይቻላል ነው ያሉት፡፡
በዮሐንስ ደርበው