የደቡብ ክልል ምክር ቤት ለ150 ዳኞች ሹመት በማጽደቅ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 3 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የደቡብ ክልል ምክር ቤት በ5ኛ ዙር በ5ኛ አመት የስራ ዘመን በ11ኛ መደበኛ ጉባኤው ለ150 ዳኞች ሹመት በማጽደቅ ተጠናቀቀ።
ምክር ቤቱ በሀዋሳ ለ 3 ቀናት ሲያካሄድ ቆይቶ ዛሬ ባጠናቀቀው በዚህ ጉባኤ÷ ከሰጠው የ150 ዳኞች ሹመት በተጨማሪ ሁለት አዋጆችንም መርምሮ አጽድቋል።
በዚሁ ወቅት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አጎ ÷በምልመላ ወቅት እጩ ዳኞቹ እድሜያቸው ከ25 አመት በላይ የሆነ፣የተሻለ የትምህርት ዝግጅት ያላቸውና በጥሩ ስነ ምግባር ረገድ በህብረተሰቡ ዘንድ የተመሰከረላቸው እንዲሆኑ ጥረት መደረጉን አብራርተዋል።
በዚህም 24 ለከፍተኛ ፍርድ ቤት እና 126 ለወረዳ ፍርድ ቤት ዳኝነት በድምሩ 150 ዳኞች በእጩነት ቀርበው ምክር ቤቱ ሹመታቸውን በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።
የምክር ቤቱ አባላት በየቦታው የሚታየው የዳኞች እጥረት ችግር እንዲቀረፍና የሴቶች ተሳትፎ እንዲጠናከር አሳስበዋል ።
እጩ ዳኞቹ ፍትህን በማስፈንና የህግ የበላይነትን በማስጠበቅ ረገድ አርኣያ ሆነው ስራቸውን እንዲሰሩ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሄለን ደበበ አሳስበዋል ።
ምክር ቤቱ የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/ መንግስት ማሻሻያ የተደረገበትን የጤና አገልግሎት አሰጣጥና አስተዳደር እንዲሁም የከተሞች ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ የሚሉ ሁለት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል።
ከዚያም ባለፈ ምክር ቤቱ የተጓደሉ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎችን በማሟላት የ3 ቀናት ውሎውን ማጠናቀቁን ከደቡብ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።